የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል በመስቀል አደባባይ ተከፈተ

የምስራቅ አፍሪካ የጥበባት እና የባህል ፌስቲቫል የመክፈቻ ስነስርዓት በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሁኔታ ተጀመረ፡፡ "ጥበባትና ባህል ለቀጠናዊ ትስስር!" በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 07-12/2014 ዓ.ም በሚካደው ፌስቲቫል የዩጋንዳ፣የቡሩንዲ፣የደቡብ ሱዳን፣የሶማሊያ ሀገራት እና የክልል እና የከተማ አስተዳደር የኪነ-ጥበባትና የባህል ልዑክ ቡድን ታድመዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላፉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ስም እንኳን ወደ እናት ሀገራችሁ በደህና መጣችሁ በማለት መድረኩ አፍሪካ ያላትን ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን ለመላው ዓለም የምናሳይበት ነው ብለዋል።

የፌስቲቫሉን መጀመር ያበሰሩት እና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመተባበር ያዘጋጁት ይህ ፌስቲቫል የምስራቅ አፍሪካን ለማዋሃድ በሚደረገውን ጥረት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና እንደሚታመን ተናግረው ለዘመናት የዘለቀውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ግንኙነትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማስቀጠል ትክክለኛ ወቅት እንደሆነ የገለፁት ክቡር ሚንስትሩ ማንም ብቻውን በመቆም ጠንካራ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ ማንም ብቻውን በመሮጥ አሸናፊ ሊሆን እንደማይችል በሚገባ ተረድተን በዓለም አቀፉ የውድድር መድረክ ላይ ሁላችንም ጠንካራ እና አሸናፊዎች እንድንሆን ያሉትን እውነታዎች መረዳት እና አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

አክለውም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተጎናጸፍናቸውን የተፈጥሮ በረከቶች ከባህላዊ እሴቶች ጋር በማጣጣም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደ ዋና ዘዴ ከመጠቀም ባሻገር እነዚህ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ንብረቶች ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎችን በኩራት የምናስጎበኛቸው ሀብቶቻችን ናቸው ብለዋል።

የባህል ዲፕሎማሲ ለኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቆጠራል ያሉት ሚኒስትሩ የፌስቲቫሉ መካሄድ ምስራቅ አፍሪካን ለአህጉሪቱ እና ለአለም አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የስበት ኃይል ማዕከል ለማድረግ ለምናደርገው ረጅም ጉዞ እንደ መነሻ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። ለዚህም በመጪዎቹ አመታት ፌስቲቫሉ በእርግጠኝነት ሁሉንም የአህጉሪቱን ሀገራት የማካተት አድማሱን እንደሚሰፋ ገልጸዋል።

በመጨረሻም የምስራቅ አፍሪካ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም የዚህ ታሪካዊ ክስተት አካል ለመሆን ላደረጉት ውሳኔ ምስጋናቸውን አቅርበው በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታቸው ፍሬያማ እና አስደሳች እንደሚሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየውን የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል እንዲሁም በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ለእይታ የቀረቡ ታሪካዊና ጥንታውያን ስብስቦችንና መጻሕፍት፣የእደ ጥበብ ውጤቶች  ተጎብኝተው ከተለያዩ ክልሎች ተዘጋጅተው ለእይታና ለቅምሻ የቀረቡ የባህል ምግቦች በቦታው የተገኙ ተሳታፊዎች መአዱን ተቋዳሽ በመሆን አምሽተዋል፡፡

Share this Post