ለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የእውቅና መስጠት መርሐ ግብር ተከናወነ
ለሀገር እና ለኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ታላቅ ባለውለታ ለሆኑት ለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ልጃቸው አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እና ወዳጅ ቤተሰባቸው እንዲሁም የሚድያ አካላት በተገኙበት የእውቅና መስጠት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ “ወመዘክር መታሰቢያ ሆኖ ከመቋቋሙ በፊት እንደ ግለሰብ የቆመ ተቋም ነበረው ብንል አንዱ ግለሰብ የሚሆኑት ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱም ከአባታቸው የወረሱትን ስራ በህትመት እና በማሰራጨት እያስቀጠሉ ያሉት ልጃቸው አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልጸዋል፡፡
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የዛሬው የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብት እና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ይጠራበት የነበረው “ወመዘክር” የሚለውን ስያሜ ከመስጠት ጀምሮ አሰባስበው የያዟቸውን መዛግብት ለተቋሙ በመስጠት እንዲሁም በሀገራችን ጥንታውያን መዛግብትና መጻሕፍት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ጭምር ያደረጓቸው እጅግ በርካታ አስተዋጽኦዎች፣በሚሰሯቸው የጽሑፍ ስራዎች ሁሉ ለአማርኛ ፊደላት ልዩ ጥንቃቄዎችን የሚያደርጉና ለሌላውም ልምዳቸውን የሚያጋሩ እንደነበሩ የቅርብ ሰዎቻቸው በመርሐ ግብሩ ላይ ምስክርነትን ሰጥተውላቸዋል፡፡
የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መዛግብት በተቋሙ ካሉ የግለሰብ መዛግብት ስብስቦች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ እና ለበርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች ተቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሆነ የሀገር ሀብት ነው፡፡
በመጨረሻም በተቋሙ የሚገኘው አዳራሽ ከዛሬ ጀምሮ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አዳራሽ ተብሎ እንደተሰየመ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ አብስረው ከአቶ አመኃ ጋር በጋራ መርቀው ክፍት አድርገው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡