ከብሔራዊ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ኦዲት ቦርድ በተዛወሩ ሰነዶች ላይ የምዘናና መረጣ ሂደት ተጠናቀቀ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በአዋጅ 179/91 በተሠጠው ስልጣን መሰረት የብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ ኦዲት ቦርድ ታሪካዊ መዛግብትን እንዲመረጡና ወደ ተቋሙ እንዲዛወሩ፤ የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱና ዘላቂ ፋይዳ የሌላቸውን ሰነዶች ደግሞ ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲወገዱ የማድረግ ስራ አከናውኗል፡፡
ከብሔራዊ ባንክ 11,640 አቃፊ ሰነዶች የውገዳ ጥያቄ የቀረበባቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 19 አቃፊ ተለይተው ከዚህ ቀደም ወደ መዛግብት ክምችት ከተዛወሩ የብሔራዊ ባንክ መዛግብት ጋር ተደራጅተው እንደሚጠበቁ ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ኦዲት ቦርድ በአጠቃላይ 23,255 የውገዳ ጥያቄ የቀረበባቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማስረጃ ሊውሉ የሚችሉ 36 ጥራዝ መዛግብት ለቋሚ ጥበቃ ተለይተው ወደመዛግብት ክምችት ገብተዋል፡፡
ይህም ተግባር ማንኛውም ሰነድ አመንጪ ተቋማት ሰነዶችን ማስወገድ እንደማይችሉና ሰነዶችን ለማስወገድ ሊታለፉ የሚገባቸውን ህጋዊና ሙያዊ ደረጃዎች አልፎ የተከናወነ በመሆኑ ለሌሎች ተቋማትም ግንዛቤን የሚያሰፋ እንደሆነ የአብያተ መዛግብትና የአብያተ መጻሕፍት ስልጠናና ምክር ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያዘጋጀውን የምስክር ወረቀት የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አባተ ካሳው አበርክተው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡