ትውልዱን የሚያንጹና የተለያዩ ይዘት ያላቸው በርካታ መጻሕፍት ተበረከቱ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው መጻሕፍትን ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት አበርክቷል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ሀገራችን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ረዥም ሂደትና ጥረትን የሚጠይቅ የመጻሕፍት ዝግጅትና መጻሕፍቱም ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ የማህደር ማስቀመጫ ሙያዊ በሆነ መልኩ ይዘጋጃል፡፡ ይህም ሀገራችን የመጻሕፍት ሀገር ናት እንድንል ያስችላል፡፡ ሆኖም ግን የቤተመጻሕፍት ሀገር አልነበረችም፡፡ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ቢኖርም በርካታ አብያተ መጻሕፍት ሀገራችን ያስፈልጋታል። ከጅምሩ ጀምሮ ለቤተመጻሕፍት ተብሎ በልዩ ሁኔታና እይታ አብርሆት ቤተመጻሕፍት መገንባቱ አስደሳች ነው፡፡ ለዚህ ለመጻሕፍት ክብር በሚመጥን ሁኔታ ለተሰራው ቤተመጻሕፍት የሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው በዋንኛነት በኢትዮጵያዊያን የተፃፉ እና በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት የተዘጋጁ መጻሕፍትን ተቋማችን በስጦታ ለማበርከት ተገኝቷል ሲሉ በአብርሆት ቤተመጻሕፍት በተደረገው ርክክብ መርሀግብር ላይ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የባህልና ኪነ-ጥበባት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ቀደምትና የኢትዮጵያን ሀገር በቀል ፍልስፍናዎችና አስተምህሮትን የያዙ የጽሑፍ ቅርሶችን ጠብቆ የያዘ የቤተመጻሕፍቶች አባት ነው፡፡ አሁንም የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎችን እየሰራ አውራነቱን ጠብቆ ያለ ቤተመጻሕፍት ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ አብርሆት ያለ ጓደኛና ወንድም በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ ለተደረገው ከፍተኛ ቁጥር ያለው መጻሕፍት አበርክቶ እያመሰገንኩ ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት የሚያስፈልገውን ሙያዊ እገዛ እንድታደርጉም እጠይቃለሁ ሲሉ የተሰማቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያበረከተውን መጻሕፍት ስጦታ ርክክብ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ የአዲስ አበባ የባህልና ኪነ-ጥበባት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሒሩት ካሳው እና አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲን በመወከል አቶ ደርብ እርገጥ አከናውነዋል፡፡

Share this Post