ተቋሙ በመደበኛ መርሐ ግብር ለተከታታይ አሥር ቀናት ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች አስመረቀ
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በመዛግብት ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና ለ22 ሰልጣኞች እንዲሁም በመሠረታዊ የቤተ መጻሕፍት ሙያ ስልጠና ለ16 ሰልጣኞች በጥቅሉ 36 ሰልጣኞች ለአሥር ተከታታይ ቀናት በመደበኛው መርሐ ግብር ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም አጠናቆ ሰልጣኞቹን አስመርቋል፡፡
ሰልጣኞቹም ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከሰነዶች ማረጋገጫ፣ ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ከትራንስፓርት ሎጅስቲክ ተቋማት የተውጣጡት በመዛግብት ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና የሰለጠኑ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲ፣ከአዲስ አበባ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ከሰንዳፋ ፖሊስ ኮሌጅና ከሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡት ሰልጣኞች ደግሞ በመሠረታዊ የቤተ መጻሕፍት ሙያ የሰለጠኑት እንደሆኑ ተጠቁሟል።
በዕለቱም የተቋሙ የአብያተ መዛግብትና የአብያተ መጻሕፍት ሥልጠናና ምክር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለ በመልዕክታቸው ጊዜው ሙያውንና ሳይንሱን አውቀውት የሚሰሩ ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያዎችን የሚፈልግ በመሆኑ ስልጠናውን በተግባር ሊያውሉት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናቸውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞች በተቋሙ የአብያተ መጻሕፍት መረጃ ሀብቶች አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ በአቶ ስለሺ ሽፈራው መልዕክት ተላልፎ ስልጠናውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸው ስልጠናው ተጠናቋል፡፡