አለም አቀፍ በዓላት ተከበሩ
በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት አለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን፣ አለም አቀፍ የወጣቶች ቀን እና አለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን በግንዛቤ ማስጨበጫና በምስጋና ፕሮግራም ተከብረዋል፡፡
ይህም በህዳር ወር ላይ የሚከበሩ በርካታ አለም አቀፍ በዓላትን በማስመልከት እንደሆነ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀገሬ መኮንን ገልጸዋል፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ የሥራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብነት አበራ የመርሐ ግብሩን ጠቀሜታ ገልጸው በተለይም እንደዚህ ተቋም አውድ ቀደምትና ረዥም ጊዜ ያገለገሉ አረጋውያን ባለሙያዎች ሙያና ዕውቀታቸውን ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
አለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሴቶች ልማት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሁላገርሽ ታዘዝ በፆታ ላይ ስለተመሰረተ ጥቃት በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን የማህበረሰብ አስተሳሰብ፣ አዝማሚያውንና እየተሰጡ ባሉ ምላሾች ዙርያ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
አለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን በማስመልከት ደግሞ የማህበረሰብ ስብዕና የሚገነባበትን መነሻ ምክንያቶች የጥናት ውጤቶችን በማስደገፍ በHope Plus Consulting & Training Services መስራች በዶ/ር ታምራት ዘላለም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል፡፡
እንደዚሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረው የአረጋውያን ቀን “ለአረጋውያን ፍቅርና ክብር” በሚል መሪ ቃል ሲከበር “የህዝብ አገልጋይነትን ክብር የተረዱና ለቀጣይ ትውልድ አርአያ መሆን ለቻሉ አረጋውያን የምስጋናና የእውቅና ፕሮግራም” በሚል ርዕስ የንብረት ስራ አመራር ቡድን መሪ አቶ ባረና በድሩ መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
በመርሀ ግብሩም ለበርካታ አመታት መ/ቤታቸውን በፍቅርና ባለመሰልቸት አገልግለው በእረፍት ዘመን ላሉ እንዲሁም አሁን በስራ ላይ ላሉ ቀደምት ሰራተኞች የምስጋናና የእውቅና ሽልማት በአቶ አብነት አበራ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት አቶ አብነት አበራ ይህንን መርሀ ግብር ያስተባበሩትን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ የስራ ክፍል አመስግነዋል፡፡