ሰባት መቶ ሺህ ብር የፈጁ መጻሕፍት በስጦታ ተበረከቱ

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት "የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!” በሚል መሪ ቃል ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ ከባቱ ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ትምህርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት እና የፓናል ውይይት መርሐ ግብር ኅዳር 20/ 2017 ዓ.ም በባቱ ከተማ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ተካሒዷል።

በዝዋይ ማረሚያ ቤት  በብሩ ተስፋ የኪነ ጥበብ ቡድን የኪነ ጥበብ ስራ ደምቆ የጀመረው በጠዋቱ መርሐ ግብር የአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳ፣ የፌደራል ማረሚያ ቤት የት/ትና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር አቶ አዝመራ አብደታ፣ የዝዋይ ማረሚያ ቤት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ም/ኮ/ር ፍቅሬ አቢዮ፣ ደራሲያን ሀያሲያን የተሳተፉበት ነበር።

በመርሐ ግብሩ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ማዕከል ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ምክትል ኮማንደር ፍቅሬ አብዩ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደተናገሩት

የስጦታዎች ሁሉ ታላቁን ስጦታ መጽሐፍ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረው ለታራሚዎች የእርምት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲያሳልፉ መጽሐፍቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

መርሐ ግብሩን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉት በፌደራል ማረሚያ ቤት የትምህርትና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር አቶ አዝመራው አብደታም በዝዋይ ማረሚያ ቤት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የህግ ታራሚዎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙና በ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከአዳሪ ትምህርት ቤት በመቀጠል የማረሚያ ቤት ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻሉ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ የሆነውን መጽሐፍት የለገሰንን የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ትውልድን ለማነጽ የሚያደርገው ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

እጃችን ታጥበን ምግብ እንደምንመገብ ሁሉ የአእምሮ ምግብ የሆኑትን መጽሐፍት በአግባቡና በሥነ ሥርዓት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ዝግጅቱን በማስመልከት ገለጻ ያደረጉት የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት የእርምት ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ውጪው ዓለም አዲስ እንዳይሆንባቸው እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እንዲህ ያሉ የንባብ ሳምንት ዝግጅቶች በማረሚያ ተቋም መጀመራቸው ጠቀሜታቸው የጎላ እንደሆነና እኛም እንደተቋም ይህንን በመረዳት የንባብ ሳምንት ያስጀመርነው ብለዋል።

አክለውም ታራሚዎች የእርምት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እና እራሳቸውን በእውቀት ገንብተው የተሻለ ሰው እንዲሆኑ እና ለከፍተኛ ፈተና እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በማሰብ የመጽሐፍት ድጋፉም እየተደረገ እንዳለም ጠቁመዋል።

ኃላፊው ተቋሙ ከንባብ ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎችን በመላው ሀገሪቷ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ተዟዙሮ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው ለዝዋይ ማረሚያ ቤት ቤተ መጻሕፍት በቁጥር 1200 መጽሐፍት በብር 400 መቶ ሺህ ብር የፈጁ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት በስጦታ እንደሚበረከቱ ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ የዝዋይ ማረሚያ ቤት ብሩ ተስፋ የኪነ ጥበብ ቡድን ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞችና ሙዚቃዎችን በማቅረብ ታዳሚውን ሲያዝናኑ ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ የማረሚያ ቤት ተሞክሯቸውን፣ በደራሲና ሀያሲ ገዛኸኝ ሀብቴ ምናብ እና ንባብ፣ በደራሲ ቁልቁሎ ኢጁ የማንበብ ክህሎትን እንዴት ማዳበር እንደሚቻል እንዲሁም በደራሲና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ወርዶፋ የመዝጊያ ስንቅ ተደርጓል።

በመጨረሻም ለዝዋይ ማረሚያ ቤት የተበረከተውን 1200 መጽሐፍት  የአገልግሎቱ የአብያተ መጻሕፍት መረጃ ሀብቶች አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው ለዝዋይ ማረሚያ ቤት ማዕከል ዳ/ዳይሬክተር ም/ኮ/ር ፍቅሬ አቢዮ አበርክተው በግጥም፣ በጥያቄና መልስ ለተሳተፉ ታራሚ ተሳታፊዎች የመጽሐፍ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

Share this Post