ተቋሙ የብሬል መጻሕፍትን በስጦታ ተረከበ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቁጥር 20 የሚሆኑ የብሬል መጻሕፍትን በስጦታ ተረክቧል፡፡
ስጦታውን የተረከቡት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በንግግራቸው እንደልብ ስለማይገኙትና ውድ ስለሆኑት የብሬል የመረጃ ሀብቶች ከልብ አመስግነዋል፡፡
አክለውም ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወደ ተቋሙ የተዘዋወሩና እንደ ሀገር መሰረት የጣሉ የብሔረሰብ ጥናት ኢኒስቲቲዩት የጥናት መዛግብት እንዳሉ እና በያዝነው አመት ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ እንደተፈራረሙ አስታውሰዋል፡፡
አሁንም በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በመኖራቸው በትብብር እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስነዜጋና መራጮች ትምህርት የስራ ክፍል የስልጠና ባለሙያ የሆኑት አቶ ይስሐቅ በቀለ በበኩላቸው መራጮች ስለምርጫ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ትምህርትና ስልጠናን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ማዳረስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ንባብ እንደመሆኑ እነዚህ የብሬል መጻሕፍት በቤተ-መጻሕፍት የሚገለገሉ ዓይነ-ስውራንን ግንዛቤ ለማስፋት ይውላል ብለዋል፡፡