ከበደች ተቀኝታለች
ገጣሚ፣ቀራጺ እና ሠዐሊ ከበደች ተክለአብ ኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከበደች ትቀኛለች በሚል ባዘጋጀው የግጥም ሰርክ ስራዎቿን አቅርባለች።
ከበደች የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውና ለአመታት በሶማሊያ በሐዋይ እስርቤት ካሳለፈችው ህይወት ጋር የተያያዘው የት ነው? የተሰኘው መጽሐፏ በድጋሚ ከመታተሙ በተጨማሪ ሱታፌ የተሰኘው አዲሱ ስራዋ በዚህ የግጥም ሰርክ መርሐግብር በተገኙት ታዳሚያን ተመርቋል።
መርሐግብሩን የከፈቱት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በንግግራቸው ከበደችን "አሳቢና ገላጭ" ሲሉ የገለጿት ሲሆን ከበደች ያለፈችበትን የህይወት ዳና፣ስለስራዎቿ መነሻና ጉዞ፣የስራዎቿ ከለርና ድምጽ ስሪት ላይ ትንታኔ ሰጥታለች።
ሠዐሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ነጻነት ገ/ሚካኤል(ዶክተር) እና ሠዐሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን(ተ.ፕሮፌሰር) በገጣሚ፣ተርጓሚና ሠዐሊ ከበደች ተክለአብ ስራዎች ላይ ሙያዊ ትንታኔና እንዲሁም ሙያዊ ቀረቤታቸውን ለታዳሚው አጋርተዋል።
የጥበብ ባለሙያዋ አዲሱ መጽሐፍ ሱታፌ በአርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ እና በጣይቱ የባህል ማዕከል አባላት በአርቲስት ሱራፌል ተካ እና አርቲስት ገበያነሽ ተመርቋል።
ገጣሚ፣ተርጓሚና ሠዐሊ ከበደች ተክለአብ በአሁኑ ጊዜ በኒዎርክ ከተማ ዘ ሲቲ ዩንቨርስቲ ኦፍ ኒዎርክ ነባር አሶስየት ፕሮፌሰር ናት።