የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለአርባምንጭ ማረሚያ ቤት የመጻሕፍት ስጦታ አበረከተ፡፡

የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለአርባምንጭ ማረሚያ ቤት የመጻሕፍት ስጦታ አበረከተ፡፡

የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲና ከጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባር በጥር 19 2016ዓ.ም በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት ውስጥ የመጻሕፍት ልገሳ አድርጓል፡፡ በመርሀግብሩ ላይም ታራሚዎች የተለያዩ የጥበብ ስራዎቻውን ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡

መርሀግብሩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አባተ ካሳው “የማረሚያ ቤት ቆይታችሁን ጣፋጫ ከሚያረጉላቹ ነገሮች መካከል መጻሕፍት ዋነኞቹ ናቸው፤ የህይወት መስመራችሁን ለመቀየር ልትጠቀሙት ይገባል“ ብለዋል፡፡

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር በሀይሉ መርደኪዮስ “አዕምሮን ከሚያሳድጉ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው መጽሐፍ ነው፤ከውጪው ዓለም ጋር እንድትገናኙና ነገን በተስፋ እንድትጠብቁ አንብቡ“ ብለው መክረዋል፡፡

ደራሲና ሀያሲ ገዛኸኝ ሀብቴ “ውስንነትና ንባብ” በሚል ርዕስ ንግግር አድርገዋል፡፡ ›

ዶ/ር ሰለሞን እንድርያስ በወጣት ጥፋተኞች ተሐድሶ ተቋም ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰሩ ሲሆን የአንድ ወጣትን መልካም ተሞክሮ በማካፈል ታራሚዎችን መክረዋል፡፡

የደንበኞች አያያዝ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፋሲል መንግስቱ በንግግራቸው ’’አርባምንጭ የቱሪዝም መነሀርያ ትሆናለች፤ በቆይታችሁ አንዱ ሌላውን ማስተናገድና ማስደሰት መልመድ አለባችሁ’’  ብለዋል፡፡

ደራሲ ዘነበ ኦላም በንግግራቸው ’’እዚህ የገባችሁበትን ቀን ምትምረቁበት ቀን ይመጣል፤ ካነበባችሁ መታሰራችሁን እስክትረሱት ድረስ ትደርሳላችሁ፤ ፊደል ያልቆጠራችሁ ደግሞ ከዛሬ ጀምሮ ማንበብ ለመልመድ የመጨረሻውን ጥረት አደርጉ’’ ብለዋል፡፡

የመጻሕፍት ስጦታውን የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ተወካይ የሆኑት አቶ አባተ ካሳው ለማረሚያ ቤቱ ሀላፊ ዋ/ኢንስፔክተር ማንዴ ማሙዴ አስረክበዋል፡፡

Share this Post