የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በጨንቻ ማረሚያ ቤት ጉብኝትና የመጻሕፍት ልገሳ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በጨንቻ ማረሚያ ቤት ጉብኝትና የመጻሕፍት ልገሳ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በጋሞ ዞን ጨንቻ ከተማ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት በመገኘት ጉብኝት እና የመጻሕፍት ልገሳ አድርጓል፡፡ ተጋባዥ እውቅ የስነ ጥበብ ሰዎች፣ ጥናትና ምርምር አድራጊዎችና በጎ ፍቃደኞች ከህይወታቸውና ከተሰማሩበት የሙያ መስክ በመነሳት ንግግር አድርገዋል፡፡

የጨንቻ ማረሚያ ቤት በደቡብ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚገኙ 15 ማረሚያ ተቋማት የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው፣ በእውቀት የተመራ፣ ማረምና ማነጽ ተግባራትን በማከናወን ተከታታይ ውጤትን ያስመዘገበ የኮሚሽኑ የማረሚያ ተቋማት አምባሳደር ነው፡፡ ግቢውም ጽዱና ማራኪ የሆነ በአፕል እና በዛፎች ልምላሜ የተሞላ ስፍራ ሲሆን ታራሚዎች በጋሞ ባህላዊ ልብስ አሸብርቀው በታራሚ አባቶች መሪነት በአከባቢው ባህላዊ አጨፋፈር በመታጀብ ለእንግዶች የክብር አቀባበል አድርገዋል፡፡

መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት ረ/ኮሚሽነር አጥናፉ አሰፋ “ስንፈልጋቹ ና ስንናፍቃቹ ነው የመጣችሁልን፤ ከሩቅ ሀገር ዕውቀትን ለመስጠትና ታራሚዎችን ለመጠየቅ መምጣታችሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስራ ነው የሰራችሁት፤እኛ እርስ በርስ ፖሊስና ታራሚ ሳይሆን የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች ወይም ቤተሰቦች ነው ምንባባለው፤ እንኳን ደህና መጣችሁልን ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመልክታቸው የሚሰጣቸውን የቤት ስራ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽህፈት ቤት ሀላፊና የተቋሙ ተወካይ የሆኑት አቶ አባተ ካሳው በንግግራቸው ስለማረሚያ ቤቱ አስደናቂነት በዚህ ዓይነት የስራ አጋጣሚ ባዩያቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙ  ማረሚያ ቤቶች ጋር በማነፃፀር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተቋሙ  ስላበረከተው የመጽሐፍት ስጦታ በተናገሩበት ወቅት ሳይነበቡ አዲስ እንደሆኑ መደርደሪያ ላይ እንዳይቀሩ ይልቁንስ አንብባችኋቸው ሲያረጁ ሌላ መጻሕፍት እንድትጠይቁን በአደራ ጭምር አሳስባለው ብለዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ ለጨንቻ ማረሚያ ቤት 350 እና ለጨንቻ ከተማ ወጣት ማዕከል ቤተ መጻሕፍት 370 መጻሕፍት በገንዘብም እንደ ቅደም ተከተላቸው 124140 ብር እና 98350ብር የሆነ ስጦታ ተበርክቷል፡፡

ስጦታውን በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የአብያተ መጻህፍት አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ያሬድ ተፈራ ለጨንቻ ማረሚያ ቤት ሀላፊ ረ/ኮሚሽነር አጥናፉ አሰፋ እና ለወጣት ማዕከል ተወካዮች አስረክበዋል፡፡

አቶ ያሬድ ተፈራ በንግግራቸው ትምህርት ከእናንተ ነው ምንወስደው፤ ከአከባቢው ንጽህና፣ ከእርጋታችሁና ከፊታችሁ ፈገግታ እንዲሁም ከአቀባበላችሁ ጀምሮ ትልቅ ትምህርት እንወስዳለን ብለዋል፡፡ የማረሚያ ቤቱን ሀላፊ ረ/ኮሚሽነር አጥናፉ አሰፋንም ስለ ማረሚያ ቤቱ አያያዝ አመስግነዋል፡፡ በማረሚያ ቤት ውስጥም የንባብ ክበባትን በመመስረት የንባብ ባህልን እንዲያጎለብቱ እንዲሁም ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሊደረግበት የሚገባውን የጋሞን ባህልና ታሪክ አባቶች ወደ ወጣቶች በዚህ ክበባት በመታቀፍ የቃል ታሪክ እንዲያስተላልፉ  ታራሚዎችን መክረዋል፡፡

Share this Post