ተቋሙ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጎበኘ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጎበኘ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ጉዳዮች አባላት ከባህልና ስፖርት ሚኒስተር ክብርት ወርቅነሽ ብሩጋ በመሆን ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም የስራ ጉብኝትና ክትትል አድርገዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በተቋሙ በመገኘት የስራ አፈጻጸምና ሂደቱን በተመለከተበት ወቅት ትኩረቱን ያደረገው በዋነኝነት በተቋሙ የሚሰጡ የቤተ መዛግብትና የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት አተገባበርና አሰጣጥን በየስራ ክፍሎቹ በመገኘት ከጎበኙ በኋላ በዋና ዳይሬክተሩና በስራ ክፍሎቹ የስራ አስፈጻሚዎች በተቋሙ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በፎቶ በታገዘ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱ ሀሳብና ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ጉዳዮች አባላት ተቋሙ የጽሑፍ ቅርሶችና የመረጃ ሀብቶችን የመጠበቅና ተደራሽ የማድረግ፣ የንባብ ልምድ ላይ በክልሎች በተለይም ማረሚያ ቤት ላይ እየሰራ ያለው ስራ፣ ግቢውን በማስዋብ ለንባብ ምቹ ማድረግ፣ ዘርፉንና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ማገዙና ሌሎችም በዉጤታማነት የሚነሱ ጉዳዮች ላይ አድናቆታቸውን በመግለጽ ይህ አፈጻጸም ወደፊት በተሻለ አቅምና ክልሎችንም በዚህ ላይ በመደገፍ እንዲጠናከር አስተያየታቸውን ስጥተዋል።
ይህ የቋሚ ኮሚቴው ምልከታ ተቋሙ እየሰራ ያለውን ስራ ለማሳወቅና የሚያስፈልገውን ድጋፍም ለማግኘት ያስችለዋል ተብሎ ይታሰባል።