ተቋሙ ሁለት የመግባቢያ ሰነዶች ተፈራረመ

የኢጵዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዛሬ መስከረም 14/2016 ዓ.ም ከባልቢስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ከሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ጋር የጋራ የስራ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የባልቢስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ማናጀር አቶ ቶማስ ስዩም፣የሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኪሩቤል ታምራት እና የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ተፈራርመውታል፡፡

የተፈራረሟቸው ሰነዶቹ ዋነኛ ይዘትንም በተመለከተ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ ሲገልጹ ሀገራችን የራሷ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ቅርስ፣ቋንቋ እንዲሁም ፊደል ያላት ሀገር ስትሆን ያንን ግን እንዴት ጠብቀን ለመጪው ትውልድ እናሻግራለን እንዴት በጋራ ሰርተን ጥንታዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ጠብቀን ለማህበረሰቡ እንዴት ተደራሽ እንደምናደርግ ከተቋማችን ጋር የሚገናኝ ስራ የሚሰሩ የግል ድርጅቶችንም ስራው ሕጋዊነትን አግኝቶ እንዲሰራም እንዳስፈለገ የሚረዳ እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በእለቱ የተፈራረሙት የማህበራቱ ስራ አስኪያጆችና ማናጀሮችም የማህበራቸውን ዓላማ እና ተግባር ለተሳታፊዎችና ለሚድያ አካላት ሲያቀርቡ የባልቢስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ማናጀር አቶ ቶማስ ስዩም ሰነዱን ከመስማማት ባለፈ የሀገራችን የሰነድ አያያዝ ከፍ እንዲልና ሪከርድና አርካይቭ ላይ ተባብሮ በመስራትና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ፤ እንዲሁም ከሌሎች የውጭ ሀገራት የቀሰሙትን ያላቸውን እውቀት እና ልምድ ለማካፈል እንደሆነ ሲገልጹ 

የሐመር ብርሃን ስራ አስኪያጅ ኪሩቤል ታምራት የቀደሙ አባቶቻችን ጥበብ ዛሬ ድረስ የምንደነቅባቸው ናቸው። ብራና አዘጋጅተው መጽሐፍ ጽፈው፣ ቅዱሳት ሥዕላትን ቀለም ከማዘጋጀት ጀምረው ሥለው አሁን ላለው ትውልድ አስተላልፈዋል።እኛም የእነሱን አርአያ ተከትለን አሁን ተቋሙ የሰጠንን እድል ተጠቅመን ከበፊቱ የተሻለ በመስራት የአባቶቻችንን ጥበብ እናስቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ከጋዜጠኞች ጥያቄ፣አሳብና አስተያየት ተነስቶ ምላሽ ተሰጥቶባቸው ለስምምነት የቀረቡት ሰነዶች ተፈርመው ርክብክብ ተደርጎባቸው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post