የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያስለማውን የተቀናጀ የቤተመጻሕፍት፣የቤተመዛግብትና የሪከርድ ማኔጅመንት ሶፍትዌር አስመረቀ

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ያስለማውን የተቀናጀ የቤተመጻሕፍት፣የቤተመዛግብት እና የሪከርድ ማኔጅመንት ሶፍትዌር /Integerated Library, Archives and Record Management System (ILARMS) ግንቦት 24/2014 ዓ.ም አስመርቋል፡፡

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱም ላይ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የሜክ ኢንተርፕራይዝ የILARMS ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር እንዳለ መኮንን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ደራስያንና የሚድያ ሰዎች እንዲሁም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እና የተቋሙ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ለዚህ ስራ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምስጋና ችረው እንደነዚህ ዓይነቱ ሶፍትዌሮች መልማታቸው የሚፈለጉ መረጃዎችን በተቀላጠፈና በቀላሉ ጊዜን ተጠቅሞ ለማግኘት እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳም በመክፈቻ ንግግራቸው  ዛሬ የለማው ሶፍትዌር እንደ ወመዘክር ያሉ በርካታ የሀገርና የግለሰብ መረጃዎች የሚገኙበት ተቋሙ ይህንን ሲስተም ተጠቅሞ መረጃ ፈላጊ ማንኛውም አካል በአካል መምጣት ሳይጠበቅበት ከሚኖርበት አካባቢ ሆኖ የሚጠቀምበት በመሆኑ ይህንን ትልቅ ስራ ለዚህ እንዲበቃ የተሳተፉትን የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማትንና ግለሰቦችን እውቅና ሰጥጠው ይህ ፕላት ፎርም ወደ ሀገራችን በመምጣት መገልገል በመጀመሩ ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሲስተም በሌሎችም የሙያ ዘርፎች እንዲለመዱ ቢደረግ መልካም አስተዳደርንም እንደሚያሰፍን ተናግረው አክለውም እንደነዚህ ዓይነት ሲስተሞችን መክፈት ብቻ ሳይሆን ተጠቅሞ በስራ ላይ ማዋል እንደሚገባም ጠቁመው የእለቱ መርሐ ግብር መከፈቱን በይፋ አብስረዋል፡፡

በዝግጅቱም የለማውን ፕላትፎርም ILARMS ፕሮጀክት ዓላማ፣ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች አስመልክቶ ከተቋሙ የILARMS ፕሮጀክት ማናጀር በወ/ሮ ኤልሳቤት አሸናፊ፣ በሜክ ኢንተርፕራይዝ የILARMS ፕሮጀክት ማናጀር በኢንጅነር እንዳለ መኮንን የILARMS ፕሮጀክት አጭር ገለጻ /ILARMS Overview/ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ት/ቤት የILARMS ፕሮጀክት ኮንሰልታንት በሆኑት በዶ/ር ወንድወሰን ሙሉጌታ የILARMS ፕሮጀክት ማኔጅመንት እና የወደፊት አቅጣጫን/ ILARMS Project management and Future prospect አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ለእይታ የቀረቡ የተለያየ ይዘት ያላቸው የጽሑፍ ቅርሶችና ፎቶ ግራፎች ተጎብኝተው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post