በበጎ ፍቃድ በሚገኙ የጤናም ሆነ የትምህርት እድሎች ላይ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ቤተ- መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ከጦር ኃይሎች ሆስፒታል ጋር በመነጋገር በአገልግሎቱ ለሚገኙ ሴት ሰራተኞች የማህጸን በር ካንሰርና የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫና የሕክምና አገልግሎት ተሰጠ፡፡
ሆስፒታሉ ይህንን ተግባር እንዲከወን ያደረገው በዕለቱ ሙሉ ጊዜውን ለአገልግሎቱ ሴት ሰራተኞች በመስጠት ሲሆን ህክምናውም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የቅድመ ካንሰር ምርመራ ተጠሪና ባለሙያ በሆኑት በሲስተር ሰላማዊት ገንታ በሽታውን በተመለከተ በቅድሚያ ጥልቅ ውይይት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ነበር፡፡
የማህጸን በር ካንሰር ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ በተሰኘ ረቅቅ ተህዋስ አማካኝነት እንደሚከሰት እና ተዋሱ የማህጸን በር ህዋሳትን በመውረር ጤናማ ያልሆነ ዕድገትና ብዜትን እያስከተለ ወደ ሌሎች የአካላት ክፍሎች በማሰራጨት የሰውነትን ተለምዷዊ ተግባር በማወክ የብዙ ሴቶችን ህይወት በመንጠቅ እንደሚታወቅም ተጠቁሟል፡፡
ሲስተር ሰላማዊት በዕለቱ በቦታው ተገኝተው ሕክምናውን ለማድረግ ለመጡ የአገልግሎቱ ሴት ታካሚዎች ግንዛቤ ሲያስጨብጡ በሽታው ስር ሳይሰድ በምርመራ ከተደረሰበት ታክሞ ለመዳን እንደሚቻል ጠቁመው አክለውም ለዚህ ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛ መንስኤ ለሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ማንኛውም የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት እንደምትጋለጥም ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ ያነጋገርናቸው የህክምናው ተጠቃሚ የነበሩ የአገልግሎቱ ሴት ሰራተኞችም ለማናቸውም ህክምና ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት በሚሔዱበት አጋጣሚ የሚያወጡትን የገንዘብና የግዜ ሁኔታ በማመዛዘን የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት እና የሴቷን ችግር ተገንዝቦ ይህንን እድል ላመቻቸላቸው የአገልግሎቱ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ እና ህክምናውን በሙያው በሰለጠኑ የሙያው አካል በእንክብካቤ እንዲሰጣቸው ላመቻቸላቸው የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ከፍተኛ ምስጋናቸውን ችረዋል፡፡
በመጨረሻም የአገልግሎቱ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሐገሬ መኮንን የስራ ክፍሉ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች፣አጫጭር ሙያዎችንና የትምህርት ስልጠናዎች በነጻና በተመጣጣኝ ክፍያ ሰራተኛውን ተጠቃሚ ለማድረግ ስራ ክፍሉ አፈላልጎ ሲያመጣ በርካታ ውጣውረዶችን አልፎ በመሆኑ በሚመጡ የትምህርትም ሆና የጤና ጉዳዮችን እንዲሁም አጫጭር የሙያ ስልጠናዎች ላይ የእድሉ ተጠቃሚ ብንሆን በማለት በአንክሮት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አክለውም ስራ አስፈጻሚዋ ይህንን ሕክምና በመጀመሪያው ቀን ላላገኙ ሴት የአገልግሎቱ ሰራተኞች ማክሰኞ ሰኔ 20/2015 ዓ.ም ጠዋት ሕክምናው እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡