የትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ምስረታ ተካሔደ

መጻሕፍት ለዕውቀት ገበታ፣መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ለታሪክ ትውስታ በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መጋቢት 2/2015 ዓ.ም በተጀመረው የመጀመሪያው ዙር የመዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ጉባዔ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከአለቃ ተክሌ ገ/ሀና አዳራሽ በተጨማሪ በደብረ ታቦር ከተማ የትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ምስረታ ተካሒዷል።

በዝግጅቱ  የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው፣ ም/ፕሬዘዳንቱ ዶ/ር መንበሩ ተሾመ፣የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተወካይ፣መምህር አገኘሁ አዳነ እና ደራሲ በሁሉም አለበል፣ ሊቃውንትና የሐይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በዝግጅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት መመስረት በራስ የመተማመን ብቃትንና ክህሎትን ለማሳደግ እንደሚረዳና ንባብ ላይ እንድትበረቱ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነውና ይህንን እድል በመጠቀም ልትበረቱ ይገባል በማለት መልዕክት በማስተላለፍ ዝግጅቱን ከፍተዋል።

በዕለቱም መምህር አገኘሁ አዳነ እና ደራሲ በሁሉም አለበል በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበብ አመሰራረትና ምንነት እንዲሁም የንባብ ባህል ላይ የራሳቸውን የህይወት ተሞክሮ ሲያካፍሉ በመርሐ ግብሩ በተሳተፉ ሊቃውንት ንባብ ላይ እና የአገልግሎቱ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀገራ መኮንን ሴቶች፣አካል ጉዳተኞችና ንባብ በሚል ገለጻ ሲያደርጉ ሀገር ላይ ያተኮሩ መልዕክት አዘል ግጥም ላቀረቡ እና ጥያቄዎችን ለመለሱ ተማሪዎች ማበረታቻ መጽሐፍት ተበርክቷል።

በመጨረሻም ለትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት ቤት እና ለሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤቶች ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት የተበረከቱት መጽሐፍት ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ተወካይ በማስረከብ በደብረ ታቦር ከተማ የተዘጋጀው መርሐ ግብር ፍጻሜውን አግኝቷል።

Share this Post