የንባብ ሳምንትና አውደ ውይይት ተካሔደ

የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር "ለንባብ ወደ ቤተ-መጻሕፍት እንሩጥ! "በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንትና አውደ ውይይት ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም አካሄደ።

በዝግጅቱም የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ውብዓለም ልዑል፣የሞጣ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አለልኝ አለኸኝ፣የሞጣ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀሐይ ወንድሙ፣ መምህር መሰረት አበጀና ደራሲ ይፍቱስራ ምትኩ፣የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ያሬድ ተፈራ እና የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የተጋበዙ የሞጣ ከተማ ነዋሪዎች ፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

በዝግጅቱም የሞጣ ከተማ ሰባቱ ዋርካ ባህል ኪነት ቡድን ባህላዊ ጭፈራ በማቅረብ ታዳሚውን ሲያዝናኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በሞጣ ከተማ ከንቲባ ተወካይ በአቶ አለልኝ አለኸኝ ሲደረግ በመልክታቸውም አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን የትምህርት ስብራት በዘንድሮ ተማሪዎች ውጤት እንደታየ ጠቁመው ለዚህ የትምህርት ስርዓታችን ማንሰራራት እና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር በመጽሐፍት የተደራጀ ቤተ መጻሕፍት አስፈላጊ በመሆኑ ወመዘክር ለሞጣ ከተማ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤቱ ከለገሰው በርካታ መጽሐፍት በተጨማሪ በዘርፉ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ያላንዳች ክፍያ ሞጣ ድረስ በመላክ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ 23 የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን ተቋሙን አመስግነው ስልጠናውን ያገኙ ሰልጣኞችም ስልጠናውን በተግባር እንዲያውሉ ሲናገሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ውብዓለም ልዑልም እንደ ከንቲባው የተሰጡ ስልጠናዎች ተሰልጥነው ብቻ የሚቀሩ መሆን እንደሌለባቸውና አንድን ሀገርና ትውልዱን ለመቀየር ትምህርት ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረው አገልግሎቱ ንባብን አስመልክቶ ቀድሞ በክልሎችና ከተሞች እየሰራ የሚገኘው ጠንካራ እና ትውልድ የማይረሳው የሚበረታታና ለለውጥ የሚታትር መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል። ከተወካይዋ በመቀጠል መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ተወካይ አቶ ያሬድ ተፈራ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ዛሬ በቤተ መጻሕፍት ሙያ ዘርፍ የበቁ ባለሙያዎች እንዳይፈልቁ ትምህርቱ በዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሀገር እየተሰጠ ባይሆንም የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ይህንኑ ክፍተት ለመሸፈን በሙያው የሰለጠኑና እውቀቱ ያላቸውን አሰልጣኞች ድጋፉን ለሚፈልጉ ክልሎች እና ከተሞች ዘርፉ ላይ ተመድበው የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሙያውን አግኝተው እንዲሰሩ በማሰልጠንና በማደራጀት እንዲሁም መጽሐፍትን በመለገስ አንባቢ ትውልድ እንጂ ጠብ ጫሪና ሀገር አፍራሽ ትውልድ እንዳይሆን እየሰራ የሚገኝ ተቋም እንደሆነም ጠቁመው አክለውም ተቋሙ ዛሬ ወደ ሞጣ ከተማ የመጣው ቤተ መጻሕፍቱን በማጠናከር እና በዘርፉ ባለሙያዎች ተደራጅቶ የተጎበኘው ቤተ መጻሕፍት ቀጣይነት ኖሮት አገልግሎት መስጠቱ ሳይቋረጥ ተደራጅተው የተቀመጡት መጽሐፍት እየጠፉም እየተቀደዱም እንዲነበቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነም ተናግረዋል።

ከአቶ ያሬድ በመቀጠል ሌላ ቦታ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በበጎ አድራጎት ተገንብቶ የሚገኘው የሞጣ ከተማ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትን በተመለከተ በአቶ ተስፋዬ አየለ ገለጻ ሲደረግ በደራሲ ይፍቱ ስራ ምትኩ አነቃቂ ንግግር በመምህር መሰረት አበጀ በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት መመስረት ስለሚሰጠው ጠቀሜታ ለተማሪዎችና በዝግጅቱ ለተሳተፉ ታዳሚያን በማቅረብ የህይወት ልምድ ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉ ዝግጅቱን የተመለከቱ አስተማሪ የግጥም ስራዎች በመምህራንና በተማሪዎች ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በስልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በተከታታይ የሚሰጠው የካታሎግ፣ ክላስፊኬሽን፣መሰረታዊ የቤተ መጻሕፍት ሙያ ሳይንስ፣የቤተ መጻሕፍት ሙያ ሥነ ምግባርና ላይብረሪ ማርኬቲንግ ስልጠና በቤተ መጻሕፍት ሙያ ስልጠና ምክር ባለሙያዎቹ በወ/ሮ አስቴር ፍሰሃ እና በአቶ ታደለ ሙላቱ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት የተሰጠውን ስልጠና ላጠናቀቁ አስራ አንድ ወንድ እና አስራ ሁለት ሴት ሰልጣኞች በጥቅሉ ለሃያ ሶስት ሰልጣኞች ከተቋሙ የተዘጋጀ የምስክር ወረቀት ሲበረከት አጠቃላይ የስልጠናውን ይዘት እና የሞጣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤቱ በአዲስ መልክ አደረጃጀቱን በተመለከተ በአሰልጣኞቹ በጋራ የተዘጋጀ ጽሑፍ ቀርቦ በወ/ሮ አስቴር ፍሰሃ ገለጻ ተደርጎ ስልጠናውን አስመልክቶ ከሰልጣኞች ግብረ መልስ ሲሰጥ ለሰልጣኞችም ከመምህር መሰረት አበጀ እጅ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በውጭም በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሞጣ አካባቢ ተወላጆችን በማነሳሳት የሞጣ የህዝብ ቤተ መጻሕፍትን ያስገነቡት አቶ ተስፋዬ አየለ የዘንድሮ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ተፈትነው አምስት መቶ እና ከዚያ በላይ ላስመዘገቡት አስር ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ሲበረከት ከአገልግሎቱም የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ሲበረከትላቸው ለባህል ኪነት ቡድን አባላት፣ሥነ ግጥም ላቀረቡ እና በጥያቄና መልስ ለተሳተፉ ተማሪዎችም ማበረታቻ መጽሐፍት በሞጣ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ፀሐይ ወንድሙ እጅ ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም ከሰባት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺህ ብር በላይ የፈጁ የተለያዩ ይዘት ያላቸው በቁጥር 4100/ አራት ሺህ አንድ መቶ መጽሐፍት ለሞጣ እና አካባቢዋ ለሚገኙ ለስምንት አንደኛ፣መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ለአራት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤቶች ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በስጦታ ተበርቶ

በአገልግሎቱ የስልጠና ባለሙያዎች የተደራጀው የሞጣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤት በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል።

 

Share this Post