ዋና ዳይሬክተር
የቤተመጻሕፍት ታሪክ የደግነት ታሪክ ነው ፡፡ ደጋግ ጸሐፍት በብዙ ትጋት ለአንክሮ፣ ለተዘክሮና ለአስተምህሮ የከተቡትን ክርታስ ሌሎች ደጋጎች በበኩላቸው ቤት ሰርተው ፣ መንበር አበጅተው ፣ ማቶት አብርተው ትውልዱ እንዲታደምላቸው ” እንካችኹ ይኽችን መጽሐፍ ብሉ ” ማለታቸው የሕብረተሰብ መሠረቱ ደግነት መኾኑን ያበስረናል ፡፡ የብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ወመዘክርን ፸፭ኛ ዓመት ስንዘክር ከዚያ በፊት ለበርካታ ዘመናት ብራና ፍቀው፣ ቀለም ጨምቀው፣ ጽፈው፣ ተርጉመው ፣ ኢትዮጵያን ” ሃገረ መጻሕፍት ” ያሰኟትን ጠቢባንና ሊቃውንት ውለታ፤ እሳት ስንወራወር መጻሕፍቱ እንዳይቃጠሉ በቃል አጥንተው ፣ ዋሻ ተከተው ትውፊታችንን ያቖዩልንን ዐቃቢያነ ታሪክ ወሮታ አብረን መዘከራችን እንዳይዘነጋ ዐደራ ፡፡ ከዚያም ከጥንት ለመጡት ብቻ ሳይኾን ወደፊትም ለሚመጡት መጻሕፍት መኖሪያና መነበቢያ ያበጁትን ታላቅ መሪ የግ.ን.ነ. የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን አባታዊ ስጦታ ከምስጋና ጋር እናስባለን ፡፡ በመጻሕፍት ብርሃን እንድናይ ለሚተጉ ኹሉ የዛሬው ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የአክብሮት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ይኩኖአምላክ መዝገቡ ዘርአብሩክ