ከ800ሺ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መጻሕፍት በስጦታ ተበረከቱ
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ 12 ት/ቤቶች፣ 1 የሕህዝብ ቤተ-መጻሕፍትና በዞኑ ለሚገኘው የቱም ማረሚያ ቤት 863,791 ብር ዋጋ ያላቸውን 2800 መጻሕፍት በስጦታ አበርክቷል፡፡
የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በንግግራቸው መጻሕፍቱ የትምህርት ማጣቀሻና የጠቅላላ ዕውቀት ይዘት ያላቸው በመሆናቸው ተማሪዎች ፣ ታራሚዎችና የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት አንባቢያን በሙሉ ሰፊውን ዕውቀትን እንዲያገኙ እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም የሰው ልጅ ቅድሚያ ንባብን ባህሉ ለማድረግ የሚቀለው በአፍ መፍቻ ቋንቋው በመሆኑ ማኅበረሰቡ በአኗኗሩና በተለያዩ ሀሳቦች ዙሪያ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጻሕፍትን እንዲጽፍ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የዞኑን አስተዳደርና ባልድርሻ አካላትን አሳስበዋል፡፡
በመቀጠል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ት/ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ በክልሉ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ከፍተኛ የማጣቀሻ መጻሕፍት እጥረት በመኖሩ የተደረገው ድጋፍ በትክክለኛና በሚያስፈልገን ጊዜ ያገኘነው ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ ደራሲያን ዕውቀታቸውንና ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን ደራሲ አንዱዓለም አባተ(ዶ/ር) የንባብ ክበባት ምስረታ ጠቀሜታን አስመልክቶ፣ ደራሲ ስንቅነህ እሸቱ ‘’ምናነበው መጻሕፍትን ብቻ ነው ወይ?’’ በሚል ሀሳብ ገጣሚ ምግባር ሲራጅ ስነ-ጽሑፍን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መጻሕፍቱን አቶ አባተ ካሳው ለዞኑ አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ጌታቸው ኪኔ፣ ለክልሉ ት/ቢሮ ምክትል ኃላፊ ለአቶ ማርቆስ ቡልቻ እና ለቱሚ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር ነብዩ ዳንኤል አስረክበዋል፡፡