የተቋሙን ስራ ዲጂታል ለማድረግ አጋዥ የሆነ ፕሮጀክት ተቀረጸ።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከባይን ሶፍትዌር ሶሉሽንስ ኤንድ ዲጂታል ስቱዲዮስ ጋር በጋራ በመሆን ለወጣቶች፣ለሴቶች፣ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለተቋሙ ተገልጋይ እና ሰራተኞች ያዘጋጁት የሁለት ወራት ስልጠና ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2019 ዓ.ም የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ የተቋሙ ሁለት ሰራተኞች በስልጠናው ማጠናቀቂያ ለተሰጣቸው የፕሮጀክት ስራ ማሟያ ያዘጋጁት ፕሮጀክት መመረጥ የቻለ ሲሆን ተቋሙ እየሰራ ያለውን የዲጂታይዜሽን ስራ የሚደግፍና የሚያግዝ እንደሆነ ታውቋል።
ስልጠናውን ከባይን ሶፍትዌር ሶሉሽንስ ኤንድ ዲጂታል ስቱዲዮስ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስራ አስፈጻሚ ናቸው።
ከባይን ሶፍትዌር ሶሉሽንስ ኤንድ ዲጂታል ስቱዲዮስ አባላት እንደገለጹት ስልጠናው በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና ዌብ አፕሊኬሽን ሲሆን በስልጠናው የተቋሙን ሁለት ሰልጣኞች ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማም ወጣቶችና ተማሪዎች በኢትዮጵያ ዲጂታል 2030 ዕቅድ ምዕራፍ ላይ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ ላይም የዲጂታል 2030 ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ተሰማ ገዳ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
የተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አገሬ መኮንን በስልጠናው ሁለት የተቋሙ ሰራተኞች እንደተሳተፉ ገልጸው በቀጣይ የስልጠና ፕሮጀክቱ የተቋሙን ሰራተኞች በበለጠ መልኩ በማካተት እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።