ካራት ከተማ"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!" በሚል መሪ ቃል የንባብ ቀን ተካደሔ።

የካቲት 24/2018 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት፣ከደቡብ ኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ቢሮ እና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመተባበር የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ቡክፌር፣የፎቶ ኤግዚቢሽን፣ሥልጠና እና የፖናል ውይይት መርሐ ግብር አንዱ የሆነው የንባብ ሳምንት በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ተካሒዷል።

በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ በተካሄደውን  የንባብ ሳምንት መድረክ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአገልግሎቱ ሥራ አመራር አቶ አብነት አበራ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከተደራጀበት 1936 ዓ/ም ጀምሮ በንባብ፣በመረጃ ማሰባሰብ እና ማደራጀት ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የቆየ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥራ አመራሩ በቀጣይ የዞኑና የክልሉ መንግሥት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው መጻሕፍት የማሟላት ስራ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውና የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ያመጣቸውን መጻሕፍት ተማሪዎች እና ማህበረሰቡ እንዲያነቡት እንዲሁም ዛሬ የሚደራጀው ቤተ መጻሕፍት ክፍት ሆኖ እንዲያገለግል ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታርኩ ኦይቻ  ንባብ የማይዳስሰው ታርክ እንደሌለና አሁን እየገጠመን ላለው የትምህርት ስብራት ሳንካ የንባብ ባህል ያለመዳበር በመሆኑ በቀጣይ የሚያነብ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አሸናፊ በርሻ ለዞኑ በተደረገው ድጋፍ በዞኑና በተማሪዎች ስም ምስጋናቸውን ቅርበዋል።

አገልግሎቱ ለኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ለ4 አንደኛ ደረጃ እና ለ2 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተለያ ዩ ይዘት ያላቸው መጻሕፍቶችን ድጋፍ አድርጓል።

በመርሐ ግብሩ ደራሲ ይታገሱ ጌትነት፣ደራሲ ዮሐንስ ገ/መድህን እና ደራሲ ገዛኸኝ ሀብቴ  ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን በ6ኛ፣በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ጥያቄና መልስ ውድድር ተካሒዶ ለተሳተፉ እና ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና መጻሕፍት ተበርክቶላቸዋል።

Share this Post