በአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም መቶ ሺህ ብር የፈጁ መጻሕፍት በሥጦታ ተበረከቱ።
የካቲት 23/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከየካቲት 22-25/2018 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ባዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ቡክፌር፣የፎቶ ኤግዚቢሽን፣ሥልጠና እና የፖናል ውይይት መርሐ ግብር ላይ ለአስራ አምስት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተመጻሕፍት ቤት፣ለአንድ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤት፣ለአርባ ምንጭ እና ለጊዶሌ ማረሚያ ተቋም በአጠቃላይ 4077 መጻሕፍት በበጀት 1,342,922 ብር የፈጁ መጻሕፍት በስጦታ አበርክቷል።
በመርሐ ግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የአርባ ምንጭ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር አለሙ ኬንቶ 130ኛውን የዓደዋ ድል በዓልን በማስመልከት ዛሬ በቅኝ ሳንገዛ አንገታችንን ሳንደፋ በነጻነት እንድንኖር ምክንያት የሆነን አባቶቻችን በከፈሉት ጀግንነት ነው።
ሰላማችንን ለማስፈን ከፊታችን ያለውን ሀገራዊ ምርጫ በዲሞክራሲ መንገድ እውን ለማድረግ የሁላችንን ድምጽ ይጠይቃል።
ማረሚያ ተቋሙ በዋናነት ሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራና የሰብዓዊ መብት መከበር ዜጎች ብቁና ምቹ እንዲሁም ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ታራሚዎች ታርመውና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በቆይታቸው ያገኙትን የሙያ ሰልጠና ተግባራዊ በማድረግ ማህበረሰባቸውን ራሳቸው ላይ ለውጥ የሚያመጡ ሊሆኑ እንደሚገባ እና ይህንኑ ለውጥ ለማምጣት ማረሚያ ተቋሙ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር አጠናክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አባተ ካሳው ለታራሚው መልዕክት ሲያስተላልፉ ዘመዶቻችሁ ሊጠይቋችሁ ሲመጡ ጥሩ የሚሉትን ምግብ ሰርተው ሳህን ቋጥረውላችሁ ይመጣሉ እኛ ደግሞ ለአእምሯችሁ ምግብ ሊሆኑ የሚችሉ መጻሕፍትን ይዘንላችሁ መጥተናል እናንተ በእርምት ጊዜያችሁ ሰዓታችሁን የሚሻማ ነገር ስለማይኖር ወጥታችሁ ከማህበረሰቡ ጋር ስትቀላቀሉ እኩል እንድትራመዱና እራሳችሁን ተወቃሽ ሳታደርጉ የፈለጋችሁት ደረጃ ለመድረስ በማንበብ ራሳችሁን እንድትለውጡ ብለዋል።
በንባብ ቀኑ ላይ ንባብን በማስመልከት ደራሲ ይታገሱ ጌትነት እና ደራሲ ገዛኸኝ ሀበቴ የንባብ ተሞክሯቸውን ሲያጋሩ፤ በታራሚዎች መልዕክት አዘል ግጥሞች ቀርበው ለግጥም አቅራቢዎች በአገልግሎቱ የሥራ አመራር በአቶ አብነት አበራ የመጽሐፍ ሰጦታ ሲበረከት ከአገልግሎቱ ለማረሚያ ተቋሙ የተበረከቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ሁለት መቶ ሰባ መጽሐፍት የአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ለኩማንደር አለሙ ኬንቶ አስረክበዋል።