ለኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበረከተለት፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት፣ ከሚመለከታቸው የተቋሙ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ጋር  ቢላሉል አል ሐበሺ ሙዚየምን ጎብኝተዋል፡፡

ቢላሉል አል ሐበሺ ሚውዚዬም በመዲናዋ ከሚገኙ ሃይማኖታዊ ሚውዚዬሞች አንዱ ሲኾን፣ የ25ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ በቦታው ላይ በተገኘንበት ወቅት የተመለከትነው ጋዜጣዊ መግለጫ እማኝ ነበር፡፡

ሚውዚዬሙ በውስጡ በርካታ የሃይማኖቱ ታላላቅ የጽሑፍ ቅርሶችን፣ የታላላቅ የሃይማኖቱ አሊሞችን (ሊቃውንት) እና የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንቶችን ፎቶ ግራፎችን እና አልባሳትን፣ ኢስላማዊ ይዘት ያላቸው መዛግብቶች እና ድርሳናትን፣ ደብዳቤዎችን፣ የሀገራችን ጥንታዊ መስጂዶች ፎቶግራፎችን፣ የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዓ.ወ.) ለኢትዮጵያ ንጉሥ የጻፉትን ደብዳቤ(ይዘቱ ታትሞ)፣ ስለ ባህል ሕክምና የተጻፉ ኪታቦችን እና ውዳሴያትን የያዙ ተፍሲሮች 'አጀሞች' እና የመንዙማ ግጥሞች ያሉበት፣ እንዲሁም ከ420 እስከ 520 ዓመታትን ያስቆጠሩ የቁርዓን ተፍሲሮች እና ከግብጽ ሀገር ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ የተሠጠ ውዳሴ ማርያም፣ የቁርዓን የኪታብ የቅርስ እና የአልባሳት እንዲሁም የቀድሞ የሀገራችን  መገበያያ ገንዘቦችን ጭምር በውስጡ የያዘ ነው። 

ሚውዚዬሙ፥ እነዚህን ወድ እና ታላላቅ ታሪካዊ ቅርሶች ለመጪው ትውልድ ተጠብቀው እንዲሻገሩ ከማድረግ ተቀዳሚ ዓላማው ባሻገር፣ ያለፈውን ታሪክ የኋሊት መለስ በማለት እንድናይ የሚያደርግ  በጥራት እና በጥንቃቄ ለጎብኚዎች በሚመች መልኩ ተጠብቀው የሚገኙበት ሀገር በቀል ተቋም መኾኑን በጉብኝቱ ወቅት ተመልክተናል፡፡

በሚውዚዬሙ ያየነው ሌላው ልዩ ተግባር፥ ወጣቶችን እና አረጋውያን ሴቶችን በዐቅም እና በኢኮኖሚ አበልጽጎ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የተቋቋሙት የማምረቻ ፕሮጀክቶች ናቸው። 

የጨርቃጨርቅ ውጤቶች ማምረቻ እና ማሠልጠኛ፣ የጫማ እና የቆዳ ውጤቶች ማምረቻና ማሠልጠኛ፣ እንዲሁም የቪድዮ ግራፊ እና ፎቶግራፍ ማሠልጠኛ ማዕከል በውስጡ በመክፈት ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ዐቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፤ ያለምንም የሃይማኖት ልዩነት ዐቅማቸውን ለማጎልበትና በኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚረዱ ሥልጠናዎችን ጎን ለጎን እየሠጠ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

በጉብኝቱ መጨረሻም፥ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ላለፉት 80 ዓመታት የሀገርን ጥንታዊ እና አኹናዊ የጽሑፍ ሀብቶችን በማሰባሰብ፣ በተገቢው መንገድ በመጠበቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ እያደረገ ላለው ዘመን አይሽሬ ተግባር፣ እንዲሁም፥ የሐረሪን ጥንታዊ የሸሪዓዊ ሕግ ብይን ሠነዶችን በዘርፉ ከፍተኛ ምሁራን በማስጠናት በUNESCO Memory Of The World በዓለም የትዝታ መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እያከናወነ ላለው ታሪካዊ ተግባር በዘርፉ በዕጩነት ለማቅረብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ቢላሉል አል ሐበሺ ሚውዚዬም 25ኛ ዓመቱን ለማክበር ጋዜጣዊ መግለጫ እየሠጠ በነበረበት መድረክ ላይ ለተቋሙ ያዘጋጀውን የዕውቅና የምስክር ወረቀት ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አበርክቷል፡፡

Share this Post