በቅዱስ ያሬድ ወርቃማ አስተምህሮ ዙሪያ ዐውደ ምክክር መድረክ ተካሔደ፡፡
በቅዱስ ያሬድ ወርቃማ አስተምህሮ ዙሪያ ዐውደ ምክክር መድረክ ተካሔደ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና፣ጥበብ፣ሥነ-ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት ጋር በመተባበር የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የቅዱስ ያሬድ ወርቃማ አስተምህሮ የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን ለመዋጀት በሚል መሪ ሀሳብ የቅዱስ ያሬድ ፍልስፍና ጥበብ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ዙሪያ ዐውደ ምክክር ተካሂዷል፡፡
በዐውደ ምክክር መርሃግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት፣ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ የዘርፉ ባለሙያዎች፣የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣የታሪክ ምሁራንና የሐይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
በዐውደ ምክክሩ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እንደገለፁት ያለውንና የነበረውን ሀገር በቀል እውቀት ቆጥሮና ቋጥሮ ማቆየት እንደሚያስፈልግ፤የሊቁ ጥበብ እና እውቀቶች ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስካሁን የቆዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪም ያለውንና የነበረውን የትምህርትና የአስተሳሰብ እውቀቶችን ቆጥሮና ቋጥሮ ማቆየት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የሊቁን እውቀቶች ለዘመናዊው ትምህርትም መጥኖ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና ጥበብ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት የቦርድ ሊቀ መንበር ዶክተር ደበበ ኢሮ በበኩላቸው፤የቅዱስ ያሬድን ጥበብና እውቀቶች እንዲሁም በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የካበቱ እውቀቶችን ለማህበረሰብ ጥቅም ማዋል እና ሀገር በቀል እውቀቶችን ማዳበርና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመቀጠልም ቁልፍ ንግግር በመጋቤ ምስጢር አፈወርቅ ተክሌ፤የቅዱስ ያሬድ ትሩፋት፣በገጣሚና ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት፤ቅዱስ ያሬድን ምን ያህል እናውቀዋለን? እና በፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ በርካታ ስራዎችን እንደሰራ እና የእርሱን ስራዎች እንዴት ወደ ዘመናዊ መውሰድ ይቻላል ወይስ እንደዚህ ነው የሚቀጥለው የሚል ጥያቄም ከፒያኒስቱ ተነስቷል፡፡
በጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ የወግ ማዕድ፤በሙዚቀኛ ሠርጸፍሬስብሐት የቅዱስ ያሬድ ዜማና ፋይዳው ወይም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፤ከኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና፣ጥበብ፣ሥነ-ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ልጅ ወንድሜነህ ለዓከማርያም፤የቅዱስ ያሬድ አገር አቅኚ እውቀቶች ዳሰሳ እና ሌሎችም በቅዱስ ያሬድ ዙሪያ በበርካታ ምሁራኖች ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ሲደረግ በዶ/ር ወንድወሰን ሙሉጌታ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ በሚል በተከፈተ ድህረ ገጽ ላይ አባል እንዴት መሆን እንደሚቻልና አባል ለመሆን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የያዘ ድህረ ገጽ ተዋውቋል፡፡
በስተመጨረሻም የቅዱስ ያሬድ አስተምሮ በሚገባ ታውቆና ተመርምሮ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም መጥቀም የሚገባውን ያህል መጥቀም እንዲያስችል የመጀመሪያውን ዓውደ ምክክር የኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና፣ጥበብ፣ሥነ-ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት፣ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት በጋራ ለማዘጋጀት ተረክበዋል፡፡