ተቋሙ በቤተ መጻሕፍት ሙያ እና በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ሙያ በመደበኛ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች አስመረቀ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በቤተ መጻሕፍት ሙያ እና በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ሙያ በመደበኛ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 71 ሴት እንዲሁም 19 ወንድ ሰልጣኞች በድምሩ 90 ሰልጣኞችን በነሐሴ 24 2016 ዓ.ም አስመርቋል፡፡
ሰልጣኞች ከአ.አ ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ ክልል እና ከደቡብ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከመንግስት ከፍተኛ የት/ት ተቋማት፣ ከአ.አ ከተማ አስተዳር ት/ት ቢሮ የተለያዩ ት/ቤቶች፣ ከግል ኮሌጆች፣ ከሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ከልዩ ቤተ መጻሕፍት እና ከልማት ድርጅቶች የተወጣጡ ናቸው፡፡
የአብያተ መዛግብትና የአብያተ መጻሕፍት ሥልጠናና ምክር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለ ባስተላለፉት መልዕክት ጊዜው ሙያውንና ሳይንሱን አውቀውት የሚሰሩ ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያዎችን የሚፈልግ በመሆኑ ስልጠናውን በተግባር ሊያውሉት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ከተቋሙ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና ከህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ተወካይ ስራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬዘር ዘውዴ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል፡፡