የወሩ ወንበር ስለአዳም ተዘረጋ

የወሩ ወንበር ስለአዳም ተዘረጋ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ሁለተኛውን የወር ወንበር ስለአዳም ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ አዳራሽ ዘርግቷል።

ልዩ የሆነ የእራሱ አጻጻፍ መለያው የሆነው የደራሲ አዳም ረታ ስራዎች ላይ ጥቂት ምልከታ ለማድረግ"አዳም: ከአለፍ አገደም_ የአዳም ረታ ስራዎች ጥቂት ምልከታ"በሚል የተዘረጋው ወንበር በአርቲስት አዜብ ወርቁ ከደራሲው ስራዎች በተወሰደ ቅንጭብ ንባብ ተጀምሯል።

የወር ወንበር መርሐግብር መስራችና በደራሲ አዳም ረታ የስነጽሁፍ ስራዎች ላይ ትንታኔ ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በደራሲው ስራዎች ላይ በሰጡት ጥቅል አስተያየት ደራሲ አዳም ረታ የኢትዮጵያ ስነጽሑፍ አንድ ምዕራፍ ነው ፤ የተጓዘበትን ስፍራ እያሳየ አየኖረ የጻፈና በተጨማሪም የእኛን የኑሮ መልክ እንደየዘመን ስፍራ በስራዎቹ አሳይቶናል ብለዋል።

አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ደራሲው ገጸባህሪያትን በቦታ፣በስልጣኔ፣በዘመን የተለያዩ የነፍስ ፍሰቶችን አስነብቦናል በሚል የአዳም ስልተ ጽሑፍን ከስራዎቹ በመውሰድ በተለይም እቴሜቴ የሎሚ ሽታ ላይ የተለያዩ ስነጽሑፋዊ፣ማህበራዊ፣ስነልቦናዊና ፍልስፍናዊ ምልከታዎች ጋር በማሰናሰን ስነጽሑፋዊ ምልከታ አቅርበዋል።

በመርሐግብሩ የስነጽሑፍ ባለሙያዎች፣ተማሪዎችና ተመራማሪዎች፣አንባቢያን እንዲሁም የደራሲ አዳም ረታ አድናቂዎች ሐሳባቸውን በማካፈል በደራሲው ስራዎች ላይ ግላዊ እይታቸውን አጋርተዋል።

Share this Post