7ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት፤ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት 7ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ ግንቦት 27/2014 ዓ.ም ተጀምሮ ለሶስት ቀናት ተካሂዷል ፡፡

“ግዕዝ ወ ጥበባት!” በሚል መሪ ቃል ለ7ተኛ ጊዜ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጅማሮውን ያደረገው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ መርሐ ግብር ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ሊቃውንት፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራር አካላት፣ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና መምህራን፣ ደራሲያን ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እና ከተቋሙ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

በዝግጅቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው ሲደረግ ፕሬዘዳንቱ በንግግራቸውም ሰፊ መልዕክት ሲያስተላልፉ ከመልዕክታቸውም ዘመናዊነት ትላንትን ትቶ ዘመናዊነትን መሻትና መተግበር ብቻ ሳይሆን የትላንቱን እያዘመኑና እያሻሻሉ መሔድ እንደሆነም አበክረው ተናግረዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡም ዘመናዊነት ላይ የሚታዩ የቀድሞውን ሙሉ በሙሉ ትቶ ከአዲስ ለመጀመር መሞከር ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተናግረው አክለውም ኃላፊው ዘመናዊነት ትላንታችን ከግዕዝ ትምህርት ማንሳት እንደሚገባና ግዕዝ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ልቦና ታሪክን የምናስታውስበት ሲሆን ሌላው ዩኒቨርሲቲዎችን ደከሙ የሚባሉት እኛነታችንን ወደ ሚያስረሱ ወደ ውጩ ዓለም ሲመኙና በደበሎ የተደበቁ እኛነታችንን ትተን ስንጓዝ ነው፡፡ ብዙ ነገራችን በብድር ከውጩ ዓለም የመጡ ናቸው፡፡ ከጥንቃቄ የሚወጣ ነው፡፡ ጥንቃቄ ስንል የተፈጠረን ነገር አጥብቆ መያዝ አባቶቻችን የያዙትን ስልትና ባህል አጠናክሮ መያዝ ያሻል ቤተክርስትያናት ትላንት ያለችውን ቅኔና ድጓ ደግማ በበንጋታው አትለውም ሁሌም አዲስ ናት ብለው በማከልም የራሳችንን ነገር አጠናክረን ልንይዘው ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከመልዕክቶቹ በመቀጠል ቅኔና ድጓ ለተሳታፊዎች በማቅረብ አእምሯቸውን በዝማሬ እንዲያድሱ ቅኔ በጸጉር ሚካኤል ቅኔ መምህር በሊቃውንት መሪጌታ በጽሐ ሲሳይ፤ድጓ የቅድስት ቤተልሔም የድጓ ምስክር መምህር በሆኑት በሊቀ ምሁራን ይትባረክ ካሣየ ቀርቧል፡፡

የዕለቱ ቁልፍ ንግግር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት በዶ/ር ሰጣርጋቸው ሲቀርብ በአለቃ ገብረ ሐና ባህል ጥናት ዳይሬክተር በመ/ር እርጥባን ደመዎዝ ደግሞ ግዕዝና ጥበባት በደቡብ ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመ/ር ስንኮሪስ አያሌው የሀገር ፍቅር በቅዱሳት ሥዕላትና በግዕዝ ድርሳናት በተመለከት ሰፋ ያሉ ሐሳቦችን የሚያነሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጥያቄ፤ሐሳብ አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸው በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በአለቃ ተክሌ ገብረሃና አዳራሽ ሲካሔድ የነበረው መርሐ ግብር ተጠናቆ በመቀጠልም ከአገልግሎቱና ከደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢ የተዘጋጁ የመዛግብትና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ለተመልካችና ለተሳታፊዎች ክፍት የማድረግና የመጽሐፍ ልገሳ በደቡብ ጎንደር ዞን በጦርነቱ ለተጎዱ አብያተ መጻሕፍት ለማገዝ ለስድስት አንደኛ ደረጃ እና ለአራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ-መጻሕፍትና ለአንድ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት በቁጥር 4000 /አራት ሺህ መጻሕፍት በብር 599‚247 /አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ብር/ የፈጁ በመለገስ የግንቦት 27 /2014 ዓ.ም. የጠዋቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡

በከሰዓት መርሐ ግብርም በሊቃውንት ዝማሬ ዝግጅቱ ተከፍቶ የተክሌ አቋቋም ማህሌታዊ ክዋኔ ፍንገጣ ኪናዊና ማህበራዊ አንድምታ በደቡብ ጎንደር የሙሾ ረገዳ ማሳየት እና ለአለሙ ሙዚቃ እርሾ የሆኑት አብነቶች በሚሉ ጥናታዊ ጸሑፎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ሐሳብ አስተያየት ተሰንዝረው ምላሽ ተሰጥቶባቸው የመጀመሪያው ቀን የጉባኤው መርሐ ግብር ተጠናቋል።

Share this Post