በአዲሱ በጀት ዓመት ተቋሙ የስልጠና ክንውን ፈጽሟል

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የቤተመጽሐፍት ባለሙያዎች በእውቀት፣ በክህሎት እና በሙያዊ ሥነ-ምግባር ታንፀው የሙያ ሳይንሱን ተከትለው መስራት እንዲችሉ እንዲሁም በሀገራችን ከትንሹ የአስተዳደር ዘርፍ እስከ ትልልቅ ተቋማት በተገልጋዮች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና መጉላላትን የሚፈጥረው የሰነድ አያያዝና አስተዳደር ላይ ስልጠናዎችን በተቋሙ እና ጥያቄ ባቀረበው ተቋማት በመገኘት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በአዲሱ የ2ዐ15 በጀት ዓመት የተቋሙ የአብያተ መዛግብትና አብያተ መጽሐፍት ስልጠና ጥናት ምርምር ዳይሬክቶሬት በሐምሌ ወር 2ዐ14 ዓ.ም በቤተመጽሐፍት ሙያ ሳይንስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጡ 23 እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 1 ሰልጣኞችን በተቋሙ ውስጥ ያሰለጠነ ሲሆን ሴቶች 17 እና ወንዶች 6 ናቸው፡፡ በነሐሴ ወር 2ዐ14 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጡ 2 ወንድና 17 ሴት ሰልጣኞች በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ያሰለጠነ ሲሆን በቤተመጽሐፍት ሙያ ሳይንስ ከደቡብ ሕዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ለመጡ 13 ወንድ ሰልጣኞች በቤተመጽሐፍት ሙያ ሳይንስ ዘርፍ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለተቋሙ በጥያቄ በቀረበ የስልጠና ፍለጎት መሠረት በቤተመጽሐፍት ሙያ ሳይንስ ዘርፍ ለ11 ወንድ እና ለ21 ሴት ሰልጣኞች በሰንዳፋ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እና ለ12 ወንድ እና ለ13 ሴት ሰልጣኞች በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በንሳ ዳዬ ካምፖስ ስልጠናን መስጠቱ የተቋሙ የአብያተ መዛግብትና አብያተ መጽሐፍት ስልጠና ጥናት ምርምር ዳይሬክቶሬት አሳውቋል፡፡

Share this Post