የሦሥት ትውልድ ታሪክ የመዛግብት ርክክብ ተደረገ

 

ዘላለማዊ የታሪክ አሻራና የዘመን ትውስታ መካነ መዛግብት የቤተሰብ ታሪካችሁ በቋሚነት ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በስጦታ ስላበረከቱ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ ቤተሰቦች የእውቅና ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ግንቦት 11/2014 ዓ.ም ተካሔደ፡፡

በዝግጅቱ ላይ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣የአንጋፋው ጋዜጠኛ የትዳር አጋር ወ/ሮ ሙሉሸዋ አበራ፣የቅርብ ዘመዶቹና የአገልግሎቱ ባለሙያዎች ሲገኙ በዝግጅቱም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዝግጅቱን በተመለከተ መልዕክት ሲያስተላልፉ በርካታ ሰዎች ጋር ትላልቅ የሀገር ታሪክን የያዙ፣ስለግለሰቦች የተጻፉ በርካታ መዛግብቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረው ግለሰቦች በጃቸው የሚገኙ ማናቸውንም አይነት መዛግብት ናቸው የሚሏቸውን ወደአገልግሎቱ ቢያመጡ ወይም ለአገልግሎቱ ጥቆማ ቢያደርጉ አገልግሎቱ ከነዛ ውስጥ መዛግብት የሚሆኑትን በመምረጥ ለትውልድ ጠብቆ እንደሚያቆይ አስገንዥበው አክለውም እንደ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ ያሉ ቤተሰቦችና ጠንካራ የትዳር አጋሮች ክብር ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

የአገልግሎቱ የሰነድና መዛግብት አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጠና የዕለቱን ዝግጅት ዋነኛ ዓላማ የመዛግብት ርክብክብ እንደሆነ ተናግረው መዛግብት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እንዴት ተለይተው እንደሚሰነዱና ለትውልድ እንዲቀመጡ መስራት የአገልግሎቱ ድርሻ ቢሆንም መረጃዎችን በማምጣት የሕብረተሰቡን ተነሳሽነትና ፍቃደኞነት ስለሚጠይቅ የዛሬው የጋዜጠኛው የትዳር አጋር ለሌሎች አርአያ ናቸው ብለዋል፡፡

ከጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ ቤተሰቦች ተሰድረው እንዲቀመጡ ለአገልግሎቱ የተሰጡት መዛግብቶች የሚሸፍኑት ጊዜ ከ1980 እስከ 2006 ዓ.ም እንደሆነና አደረጃጀቱንም በተመለከተ በአቃፊ 25 በፋይል 135 እንደሆኑ በአገልግሎቱ የመዛግብት አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አዛርያስ ኃ/ጊዩርጊስ ተቀምረው በዕለቱ ለነበሩ ተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡

በመጨረሻም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ከአገልግሎቱ የተዘጋጀ የእውቅና ምስክር ወረቅ ለጋዜጠኛው የትዳር አጋር ለወ/ሮ ሙሉሸዋ አበራ በማበርከት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post