የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት “መጻሕፍት የእውቀት ጮራ፤ መዛግብት የታሪክ አሻራ” በሚል መሪ ቃል  ከባሌ ዞን ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት እና ከመደወላቡ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በባሌ ሮቢ እና በባሌ ጎባ ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 02 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው የንባብ ሳምንት መርሀ ግብር ላይ  አንዱ አካል ከሆነው በባሌ ጎባ ግንቦት 01 ቀን 2014 ዓ.ም “የቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ሚና ትውልድን ከመገንባት እስከ ማስተሳሰር “ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነው፡፡  
መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የጎባ ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳ መሐመድ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የካበተ ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያ አቶ አብይ ብሩክ “የሪከርዶች እና የመዛግብት ምንነትና ጠቀሜታ”፣ አቶ አባይነህ ካሳ “የባሌ መዛግብት በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት”፣ ወ/ሮ አለም ጌታቸው “ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት መለያ ቁጥር እና የመጽሐፍት አዘገጃጀት መርሆዎች ምንነትና ጠቀሜታ”፣ አቶ ስለሺ ሽፈራው “የጽሑፍ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ዛሬና ነገ” በሚሉ ርዕሶች በአቶ መሐመድ ኬኪ አወያይነት የውይይት መነሻ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረቡት ጽሑፎች ብሎም ይህ የንባብ ሳምንት መዘጋጀት ጠቀሜታን በመግለጽ አስተያየታቸውን ከሰጡት ተሳታፊ አንዱ የሆኑት አቶ አወል አብዱልጀዋር  የጎባ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ በወረዳው ከፍተኛ የትምህርት መጻሕፍት እጥረት መኖሩንና ተማሪዎችም በዚህ በጣም ተማረው በነበሩበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ለእነዚህ ት/ቤቶች ላደረገው የመጽሐፍት ስጦታ እጅግ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልፀው በዕለቱ የቀረቡት የውይይት መነሻ ጥናታዊ ጽሑፎች ተሳታፊዎች በሰነድ እና በመዛግብት ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች እንደመሆናቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው እና የተገኙት አመራሮችም የሰነድና የመዛግብት ሀገራዊ ፋይዳን በመረዳት ባለሙያዎች እንዲበቁ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግና በጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም በባሌ ያሉ ተገቢውን ትኩረት ያላገኙ የጽሑፍ ሀብቶች ላይ እንዲሠሩ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በእለቱ ከቀረቡት በተቋሙ ከሚገኙት የባሌ መዛግብት መሐል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ከሀገር ግዛት ሚኒስቴር ጋር የተጻጻፉት  ደብዳቤዎች  መነሻ በማድረግ ሲሆን የውይይት መድረኩ የተከናወነበት ግቢና አዳራሽ  የአሁኑ የጎባ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የባሌና የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት አስተዳደር በነበሩበት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረው ተቋም መሆኑን ለታዳሚያን አሳውቀዋል፡፡
 

Share this Post