“መጻሕፍት የዕውቀት ጮራ ፤ መዛግብት የታሪክ አሻራ” በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት፣ ቡክፌር፣ አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት መድረኮችን በባሌ ሮቤ እና በባሌ ጎባ ከተማ አካሄደ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት እና ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “መጻሕፍት የዕውቀት ጮራ ፤ መዛግብት የታሪክ አሻራ” በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 02 ቀን 2014 ዓ.ም የንባብ ሳምንት፣ ቡክፌር፣ አውደ ርዕይ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት መድረክ በባሌ ሮቤ እና በባሌ ጎባ ከተማ አካሄደ፡፡ የመክፈቻው መርሃ ግብር ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በተለያያዩ ስዓቶች በሁለቱ ከተማ ማድረግ የቻለ ሲሆን ፤ በሮቤ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀዳ ስንቄዎች ( Hadhaa Siinqqe)፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ፣ የከተማው ወጣቶች፣ ተማሪዎችና መምህራን በተገኙበት በከተማው አደባባይ በደማቅ ሁኔታ ተክፍቷል፡፡ በዕለቱ የሮቤ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሀሰን ሱልጣን ተግኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልዕክታቸውም የንባብ ባህልን ማስረጽና ማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት ቤተመጻህፍት አግልግሎት በዚህ መስክ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ የድርጅት ኃላፊ አቶ ዲባባ ረጋሳም የመርሐ ግብሩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤የጽሑፍ ቅርሶችን መጠበቅ፣ የንባብ ባህልን ማዳበር የሁልጊዜም የትኩረት ነጥብ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በጎባ ከተማ በተካሄደው የመክፈቻ እና የመጻሕፍት ስጦታ መርሐ ግብር የከተማው ከንቲባ አቶ ተሻለ ዲሳሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ የንባብ ባህል መዳበር ለሀገራችን ሰላም ዕድገት መረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኮኖ አምላክ መዝገቡ በሁለቱም ከተማ በተደረገው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በንግግርቻውም የሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች የንባብ ባህልን ለማስፋፋት ቀጣይነት ያለው ሥራ መሰራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በመድረኩ ከ500,000 (ከአምስት መቶ ሺ ብር) በላይ ያወጡ መጻሕፍት ለትምህርት ቤቶች እና ለከተማው የህዝብ ቤተመጻሕፍት በስጦታ ሊተላለፍ ችሏል፡፡ በእለቱ ከቀትር በኋላ በሮቤ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ የትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ምስረታና የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ በደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህሩ ቁልቁሉ ኢጆ እና በደራሲ ደጀኔ ኤጄሬ ለተማሪዎች እና መምህራን ስለ ንባብ አስፈላጊነትና የንባብ ክበባት አመሰራረት ሂደት እና ጠቀሜታ የማነቃቂያ መልዕክት ሊተላለፍ ችሏል፡፡ በመድረኩ ከ600,000 (ከስድስት መቶ ሺ ብር) በላይ ያወጡ መጻሕፍት ለትምህርት ቤቶች እና ለከተማው የህዝብ ቤተመጻሕፍት በስጦታ ሊተላለፍ ችሏል፡፡

አገልግሎቱ በሚያዚያ 30 መርሐ ግብሩ ለሮቤ ከተማ ማረሚያ ቤት ግምታቸው ከ160,000 (ከአንድ መቶ ስልሳ ሺህ ብር) በላይ ያወጡ መጻሕፍት ለማረሚያ ቤቱ አበርክቶ በዕለቱም በቦታው በተጋበዙ ደራሲያን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለፈልገ ሥነ-ጥበብ ዋና ዳይሬክተር እና ገጣሚ አገኘው አዳነ እና በሚመለከታቸው አካላት ለታራሚዎች አነቃቂ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

ግንቦት 1 ቀን በሮቤ ከተማ አባ ገልማ አዳራሽ ባህል አዳራሽ የእስላምና የጽሑፍ ቅርሶች ታሪክን ከማስጠበቅ እስከ ማስቀጠል በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደውን የፓናል ውይይት በንግግር የከፈቱት የሮቤ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አለም ጸጋ ሲሆኑ፤ ኃላፊዋ በንግግራቸው እንዳሉት የጽሑፍ ቅርሶች መጠበቅ የጥናትና ምርምር ሥራን ተጨባጭ ለማድረግ ከፍተኛ አስተጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊዋ አክለውም የእስልምና የጽሑፍ ቅርሶች ካላቸው ታሪካዊነት ባሻገር የሀገርም ቅርስም ናቸው ብለዋል፡፡ በዕለቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ሀሰን መሀመድ እና ከመደ ወላቡ ዪኒቨርሲቲ ዶክትር ከፍያለው ተሰማ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በውይይቱም እስላማዊ የጽሑፍ ቅርሶችን መጠበቅ ሀገራዊ ታሪካችንን ጠበቀን ለትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ በአደጋ ውስጥ የሚገኙ የጽሑፍ ቅርሶችንም መታደግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን አጽንኦት ተስጥቶታል፡፡ በዚሁ ዕለት ምሽት በጎባ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ የመንዙም ሥርዓት አተገባበር የሚያሳይ መርሐ ግብር የተከናወነ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ የተከበሩ ሼህ መሀመድ አወል ተገኝተው ሥርዓቱን መርተውታል፡፡ በመርሐ ግብሩም በወልቂጤ የዘቢሞላ ሙዚየም መስራችና ባለቤት ሼህ መሀመድ አሚን ተገኝተው ሥርዓቱን ተካፍለዋል፡፡ በመርሐ ግብሩም የመንዙማ ሥርዓት ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ባሻገር ባህልዊና ትውፊታዊ ይዘት ያላው በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ ያለበት መሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡

Share this Post