በተቋሙ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሑፎችና የህግ ማዕቀፎች ላይ የምክክር መድረክ ተካሔደ

መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአገልግሎቱ የአብያተ መዛግብትና አብያተ መጻሕፍት ጥናትና ምርምር ስልጠና ዳይሬክቶሬት የስራ ክፍል ከሌሎች የአገልግሎቱ የስራ ክፍሎች ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎችና የህግ ማዕቀፎች ላይ የምክክር መድረክ ተካሒዷል፡፡

የምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ባለሙያዎች በአቶ አባይነህ ካሳ፣ በአቶ አባተ ካሳው፣ በአቶ ግርማ አበበ እና በመ/ር ካሳዬ ስሜ ተዘጋጅተው የቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች "የክልል አብያተ መዛግብትን ለማቋቋም ያለው አስቻይ ሁኔታ" ፣ " የባህል ሕክምና በኢትዮጵያ" ፣ " የንባብ ባህል ማስተዋወቂያና ማስፋፊያ ስልቶች በኢትዮጵያ የተመረጡ የሕዝብ አብያተ መጻሕፍትና ትምህርት ቤቶች ዳሰሳ"፣ "ምርጫ በኢትዮጵያ፤ በምርጫ ዙሪያ በተቋሙ ስብስብ የተፈጠሩ መዛግብት ዳሰሳ" የተሰኙ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲሁም "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የመረጃ ሀብቶች ለማስጎብኘት የሚያስችል የጎብኚዎች ማንዋል"፣ "የንባብ ባህል ማስተዋወቂያና ማስፋፊያ ስትራቴጂ ስልቶች ሰነድ"፣ "የዕቅድ ስራ ሂደት ሪከርዶች ማቆያ የጊዜ ሰሌዳ" የሚሉት የህግ ማዕቀፎች ከቀረቡ በኋላ በተወያዮች ለመድረኩ የተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የዳበረ ገለፃና ምላሽ ተደርጎባቸዋል፡፡

የህግ ማዕቀፎቹ የምክክር መድረኩ ላይ የተሰጡት አስተያቶች ተካተውበት በሚገባ ተጠናቅሮ በአገልግሎቱ የበላይ አመራሮች /ማኔጅመንቱ/ ሲያፀድቁት ወደ ትግበራ በመዋል በተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች የሚታየውን የተለያየ አይነት ለጎቢኚዎች የሚደረግ ገለፃ እና ማስተዋወቅ ወጥነት ያለውና አጥጋቢ ግልጋሎት ያለው የመረጃ ፍሰት እንዲኖር፤ ከዕቅድና ሪፖርት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ሰነዶች የመወገጃና ወደ መዛግብትነት የመቀየሪያ ጊዜያቸው ተለይቶ እንዲቀመጥ የማድረግና የንባብ ባህል ለማዳበር የሚሰሩ አካላት አሁን ከሚሰሩት ስራ ባሻገር የጋራ መነሻ ኖሮ ያለውን እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲሆን ከማገዙ በተጨማሪ ሌሎች ተቋማትም ከዕቅድና ሪፖርት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ሰነዶች እና የንባብ ባህል ለማዳበር የሚሰሩ ስራዎችን በተመለከተ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይም በተሳታፊዎቹ አብያተ መዛግብትና አብያተ መጻሕፍትን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማቋቋም ያለውን የዘርፉ ችግሮች ላይ እንደ ተቋም እና እንደ ስራ ክፍል ሊሰሩ ይገባል ተብለው የታሰቡ ነጥቦች እንዲሁም የተሰሩት ጥናታዊ ጽሑፎች በተሻለ መልኩ ዳብረው ሰፋ ባለ መድረክ እና መርሐ ግብር ላይ ሊቀርቡ እንደሚገባቸውና ለዛም የሚያበቃቸው ሙያዊና ምልከታዊ አስተያየቶች ሲሰጡ በቀረቡት የህግ ማዕቀፎች ላይም ቢታይና ቢካተቱ የበለጠ ያጎሉታል የተባሉ ጉዳዮች በተሳታፊዎች ተጠቁመዋል፡፡

 

Share this Post