ታሪካዊ ዐውደ- ርዕይ ተከፈተ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሚያዝያ 27 የሚከበረው በተለምዶ የአርበኞች መታሰቢያ በዓል የሚባለውን የሚያዝያ 27 የኢትዮጵያ የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ “አርበኞቻችን ለዛሬ ነፃነታችን መሠረት!” በሚል መሪ ቃል ለ81ኛ ጊዜ የሚከበረውን የድል በዓል ታሪካዊ ዐውደ - ርዕይ በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘው ክፍት ቦታ ላይ ከሚያዝያ 26 ቀን 2ዐ14 ዓ.ም ጀምሮ ተዘጋጀቶ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል፡፡

በዐውደ - ርዕዩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ኘሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፣የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እና የአገልግሎቱ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

ዐውደ-ርዕዩን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ኘሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ሲከፍቱ በንግግራቸውም አርበኞች የሀገራቸውን ክብር፣ሉዓላዊነት እና ነፃነት ብሎም ዝናና ማንነት ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋና የሔዱበትን ርቀት በማንሳትና ከአሁኑ ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ጋር ያለውን ትስስርና ትውልዱ ከቀደሙት አርበኞች ሊቀስምና ሊተገብረው ስለሚገባው ምግባርና ኃላፊነት በሚገባ አብራርተዋል፡፡

አክለውም በሀገራቸው የሚሰማቸውን ቁጭትና መንገብገብ ገልፀው አገልግሎቱ ለዚህ ቀን ክብር በመስጠት ይህን ትልቅ ዐውደ - ርዕይ በማዘጋጀቱ ምስጋና እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

Share this Post