Back

የንባብ ሳምንትና አውደ ርዕይ በጎንደር ከተማ ተካሄደ

የካቲት 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ከየካቲት 2-7/2011. ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሁለተኛውን የንባብ ሳምንትና አውደ ርዕይማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋልበሚል መሪ ቃል በጎንደር ከተማ አካሄደ፡፡

ኤጀንሲው ኋላ ቀር የሆነውን የህዝባችንን የንባብ ባህል ለማሳደግ ከክልሎች ከከተማ መስተዳደሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ካስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ የንባብ ሳምንታት፣የመጽሐፍት አውደርዕይ እና አውደ ትዕይቶች ማካሄድ ሲሆን ከነዚህም በተጨማሪ በጉዳዩ ዙሪያ በሚስተዋሉት ተግዳሮቶች ላይ የተደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎችን መሰረት በማድረግ በሚያዘጋጃቸው የፓናል ውይይቶች ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር መፍትሄ ማፈላለግ ነው፡፡

ስራው አድካሚና የበርካታ ሰዎችንና ድርጅቶችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ ጉዳዩ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ስለሆነ በባለቤትነት የሚይዘው አካል ይፈልጋል፡፡ እስካሁን ይህንን ለትውልድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳይ  ስራዬ ብሎ የመደበኛ እቅዱ አካል አድርጎ በትኩረት የሚንቀሳቀስ አካል አለመኖሩ የተጀመሩት ስራዎች ቀጣይነት እንዳይኖራቸውና የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ሆኗል፡፡

ታዲያ ይህንኑ የተያዘ ተግባር ለማስቀጠል ኤጀንሲው ከትምህርት ቢሮዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ ከልዩ ልዩ የሙያና የሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራቱ ጥሩ አጋር እና ውጤት አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ከተካሄዱት የንባብ ሳምንታት ባገኛቸው ልምድና ተሞክሮ እየታገዘ ፍሬያማ ፕሮግራሞችን በማከናወን ዘንድሮም የሁለተኛ ጊዜ ዝግጅቱን በጎንደር ከተማ የንባብ ሳምንት፣ የመጽሐፍት አውደ ርዕይ፣አውደ ትዕይንትናየፓናል ውይይት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አካሂዷል፡፡  

በጎንደር ከተማ የተካሄደው የንባብ ሳምንት፣ የመጽሐፍት አውደ ትዕይንትና የፓናል ውይይት ሂደት እና ስለጎንደር ጥቂት እንበላችሁ

በአማራ በብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ ውስን የሜትሮፖሊቲያን ከተሞች አንዷ የሆነቸው ጎንደር በአሁኑ ወቅት የሰሜን ጎንደር ዞን ርዕሰ ከተማ ናት፡፡ከተማዋ የበርካታ ግብረ-ህንጻዎች፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የኪነጥበብ፣ የንግድና የትወና ማዕከል የነበረችው የጎንደር ከተማ በአጼ ፋሲለደስ ዘመን በ1628ዓ.ም. እንደተመሰረተች ይነገራል፡፡

ጎንደር ምንም እንኳን የታሪክ፣ የጥበብ፣ የፍልስፍና እና የዕውቀት መሰረት መሆኗን የሚመሰክሩ በርካታ ቅሪቶች ቢኖሯትም አሁን ላይ ያለው ትውልድ የቀደመውን አባቶቹን ጥበብ አንብቦ ለማወቅና የበለጠ ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይህ በጎንደር ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገራችን ያለ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከዚህም በላይ ጎንደር በርካታ የጽሑፍ ሐብቶች የተፈጠሩባትና የተከማቹባት እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ይሁንና እነዚህን ለጥናትና ምርምር ማዋልና ጠብቆ በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረ ስራ አይታይም፡፡

ኤጀንሲው እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታትና የንባብ ባህላችንን ለማሳደግ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት አውደ ርዕይና የመጽሐፍት ሽያጭ እንዲሁም የፓናል ውይይቶች አካሂዷል፡፡ በዕለቱም አውደ ርዕይና የመጽሐፍት ሽያጩ በተለምዶ ፒያሳ በመባል በሚታወቀው ሰፊ ሜዳ ላይ ተካሂዶ ተጠቃሚው በቀላሉ እንዲጎበኘው እድል ፈጥሯል፡፡

መክፈቻውም በተማሪዎች ሰልፍና ከልዩ ልዩ ክፍሎች በተጋበዙ እንግዶች በከተማው ነዋሪዎችና  በባህል ኪነት ቡድን ጨፈራ ደምቆ ነበር፡፡ የከተማዋ ከንቲባ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኃላ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ዝግጅቱን አስመልከቶ ለታዳሚው ንግግር አድርገዋል፡፡

በመቀጠልም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ መልዕክት አስተላልፈው በጋራ ሪቫኑን በመቁረጥ ኤግዚብሽኑና የንባብ ሳምንቱ መከፈቱን በይፋ አብሰረዋል፡፡ የክብር እንግዶችና ታዳሚዎች ኤግዚብሽኑን ተዘዋውረው ሲጎበኙት፡፡

በሌላ በኩል የዝግጅቱ አካል የሆነው የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር  በጎንደር ሲኒማ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡ ይህም ዝግጅት በጣም አዝናኝና አስተማሪ ነበር፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ተሰጥኦዎቻቸውን በግጥምና በመነባንብ አቅርበዋል፡፡ ደራሲ ዳንኤል ወርቁ እና አንዱአለም አባተ የሕይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች አካፍለዋል፡፡ ተማሪዎች የማንበብ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩና በውስጣቸው ያለውን ይህንን ተሰጥኦ እንዲያሳድጉት አበረታተዋል፡፡ በመጨረሻም ኤጀንሲው ለማበረታች ለተወዳዳሪዎች ያዘጋጀላቸውን የመጽሐፍት ሽልማት በአቶ ያሬድ ተፈራ አማካይነት አበርክቶላቸዋል፡፡

ወጣቶችን ከጫት ሱስ ወደ ንባብ ሱስ ለማሻገር  የተዘጋጀ መድረክ በእንፍራንዝ

እንፍራንዝ ከጎንደር ከተማ በስተደቡብ ምስራቅ በ62ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ እንፍራንዝ ጥንታዊና ምናልባም በእድሜ የጎንደር ታላቅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ከተማዋ አጼ ሰርጸ ድንግል በአደራ ያስቀመጧት ይመስል ባለችበት ሆና እድሜዋን ትቆጥራለች፡፡ የዛሬን አይበለውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን አገራትን አቋርጠው ለሚሄዱ የጥንት ነጋዴዎች ማረፊያ ነበረች ይባላል፡፡ እንፍራንዝ አለማደጓ ብቻ ሳይሆን በበሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ የጫት ምርት ማዕከል ሆና ወጣቶቿን የሱስ ተገዢ ማድረጓ ያሳዝናል፡፡ የተፈጥሮ አየሯና አፈሩ ለአትክልት፣ ፍራፍሬና ለተለያዩ አዝእርት ምቹ ቢሆንም ማሳዎቿ አረንጓዴውን አደንዛዥ ቅጠል /ጫት የሙጥኝ ብለዋል፡፡

ይህ ችግር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመጣ ቢሆንም ዛሬ ላይ በቀላሉ የሚፈታ አይመስልም፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይህንን የማኅበረሰብ ችግር ለይቶ በማቅረቡ ከመርሃ ግብራችን ውስጥ አንዱ የፓናል ውይይት በዚህ ስፍራ እንዲካሄድ ተስማምተን ወደዚው ተጉዘናል፡፡ ከጫት ሱሰኝነት ወደ ንባብ ሱሰኝነት መሸጋገር የሚኖረው ፋይዳ በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ በተደረገ ጥናታዊ ጽሁፍ መነሻነት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ አምራች ሃይል የሆነውን ወጣት ለማዳን የወረዳው አስተዳዳሪ መምህራንና ህብረተሰቡ በዚህ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣቱ የማንበብ ባህሉን ለማሳደግ እንዲረዳው ኤጀንሲውና ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጁትን የመጽሐፍት ስጦታ ለትምህርት ቤቶች አበርክተዋል፡፡

በመጨረሻም ታዳሚዎች ከከተማዋ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ጥንታዊውን የጉዛራ ቤተመንግስት ጎብኝተዋል፡፡ይህ ቤተመንግስት አጼ ሰርጸ ድንግል የአባታቸውን የአጼ ሚናስ ሞት ተከትሎ ስልጣን ከያዙ በኋላ ከ1555-1587/89ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተገነባ ይታመናል፡፡  ቤተመንግስቱ ከፍ ባለ ኮረብታማ ስፍራ ላይ የተገነባ በመሆኑ የተንጣለለው የጣና ሃይቅ በቅርብ ርቀት ቁልቁል ይታያል፡፡ ግንቡ በኢትዮጵያዊያን እና ከውጭ በመጡ የህንጻ ሙያተኞች በአካባበው ከሚገኝ ድንጋይ፣እንጨትና ኖራ የተሰራ እንደሆን ይመሰክራል፡፡ ይህ ህንጻ በአካባቢው ከተሰሩ ሁሉ ቀደምት እንደሆነ ስለሚታመን ከእሱ በኋላ ለተነሱት ነገስታት እንደ ሞዴል ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ እነዚያ ደጋግ ሊቃውንቶች ባይኖሩም ቤተመንግስቱ ዛሬም ለምስክርነት በዜጎች መካከል ቆሞ ታላቅነታቸውን ይመሰክራል፡፡ እኛንም ይታዘባል፡፡ እነዚያ በዚህ ግንባታ ላይ የተጠበቡ እጆችና ይህንን ዲዛይን ያፈለቁ አእምሮዎች ግን የሚገልጻቸው ጠፋ እንጂ በመጽሐፍት ውስጥ ተደብቀዋል፡፡ ለዚህም ነው እናምብብ ብለን የምንመክረው፡፡ ስናነብ እንጠበባለን፣ ስናነብ በእውቀት እንበለጽጋለን፡፡ስናነብ ባለፈው መሰረት ላይ አሻራችንን አኑረን መጪውን ትውልድ እናወርሳለን፡፡ የዚህን ዓለም እውቀት ጠቅልሎ የያዘው መጽሐፍ ነውና መጽሐፍትን እንግለጽ፡፡ ማንበብን ባህላችን እናድርግ፡፡ያኔ እንደ አባቶቻችን ጠቢባን እንሆናለን፡፡


News Archive News Archive

— 20 Items per Page
Showing 1 - 20 of 21 results.